በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመን አጥቢያ አብያተ
ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን የተማኅጽኖ
ደብዳቤ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለዉ «ከሁሉም ግን ፍቅር ይበልጣል።»
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በውስጧ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ቤተ
እምነቶች ጋር እንኳ ፍቅርን በማስቀደም በመፈቃቀርና በመከባበር በክርስቶስ ራስነት፣
በሐዋርያት አስተምህሮና እምነት መሠረት ላይ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ስታፋጥን
ዘመናትን አስቆጥራ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እኛ ካለንበት ዘመን ደርሳለች። የቤተ
ክርስቲያኗ ሐዋርያዊ ጉዞ በርግጥ ጥንትም ቀላል አልነበረም። ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት
የገጠሟት ፈተናዎች በአመዛኙ ከዉጭ የመጡ እንደመሆናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ
የእምነት አባቶች በጽናትና በሃይማኖት ተጋድሎ አልፈውት ዛሬ ታሪክ ሆኗል። የዛሬዋ
ቤተ ክርስቲያናችንም ከመንጋዉ እረኛ ስያሜ ጋር በተገናኘ በተለይም ላለፉት ሃያ አንድ
ዓመታት እጅግ አሳዛኝ ሂደትን አሳልፋለች። ዛሬም የሚሰማዉ ሁሉ ፆሩ እንዳልበረደ
ያመለክታል። ይህ የዉጭ ተፅዕኖ ብቻ ነዉ ለማለት እንዲከብድ የሚያደርገዉ ደግሞ
አሁንም ከዚሁ የፈተና አዙሪት መዉጣት እንዳትችል የተደነቀረው ውስጣዊ መሰናክል
መኖሩ ነዉ።
በፓትርያርክ ስያሜ መግባባት ጠፍቶ የሀገር ውስጥና ስደተኛ ሲኖዶስ በሚል
አባቶቻችን መለያየታቸዉና ይልቁንም እስከመወጋገዝ መድረሳቸው ኅሊናችንን
ሲፈታተነው ቆይቷል። ይህን የመለያየት መንፈስ ይሰብራል የተባለ የእርቅ ሰላሙ
ውይይት በዳላስ መጀመሩን ሰምተን መንፈሳችን ነቅቶ ፈጣሪያችን ፍሬዉን እንዲያሳየን
ስንማፀንም ሰነበትን። የእርቀ ሰላሙ ዉይይት በይደር ተቀጥሮ ሳለ ውጤቱ ሳይታይ
በሀገር ቤት ለፓትርያርክ ስያሜ እጩ መረጣ ብሎም ዝግጅት መኖሩን መስማት፤
የዚህች ቤተ ክርስቲያን ልጅ ነኝ ብሎ በጽናት ለሚቆም ኦርቶዶክሳዊ ሁሉ ምን ያህል
አስደንጋጭና አንገት አስደፊ እንደሆነ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም።
ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት ካህናትም ሆኑ ምእመናን የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት
ተጠብቆ ማየት ዋና ምኞታቸው ብሎም እፎይታ ስለሆነ ነው። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን
በቀጣይም አዳዲስ ገለልተኞች አብያተ ክርስቲያናትና መንፈሳዉያን ማኅበራት
እንዳይፈጠሩም ስጋት አሳድሯል።
ዘንድሮ ሰላሳኛ ዓመቷን የምታከብረዉ፤ በዘመነ ስደት (ደርግ) በዓለም ዙሪያ
ለተቋቋሙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ቀዳማዊት ፋናወጊ የሆነችው በጀርመን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክስቲያን ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ትኩረቷን
በኦርቶዶክሳውያን አንድነት ላይ ብቻ በማድረግ በዚህ ሀገር የሚኖሩ ምእመናንን
አሰባስባ ቆይታለች፤ አሁንም በእምነት ጽናት ስለ አባቶች ኅብረትና ስለ ቤተ ክርስቲያን
አንድነት ትሰብካለች። ለዚህም ነው ከስድስተኛዉ ፓትርያርክ ምርጫ አስቀድሞ
ሊታሰብበት የሚገባው በአባቶች መካከል የዶግማ ልዩነት ስለሌለ እርቀ ሰላም
ይዉረድ፧ አንድነት ይቅደም የሚል ጥሪዋን ደግማ ደጋግማ የምታስተላልፈው።
«እርስ በእርሱ የሚቃወም መንግሥት አይጸናም» እንዳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤
ፍቅርና ትኅትናን ብሎም አንድነትን ለእኛ ለልጆቻቸዉ የሚሰብኩ አባቶቻችን
እንደመሪያቸዉና እነሱም በሐዋርያነት እንደሚከተሉት ፈጣሪያቸዉ ቃልን በተግባር
የሚገልጹ መምህራን እንዲሆኑላትም ትሻለች። ከፍቅር የሚበልጥ አንዳች ነገር የለምና፤
ሥልጣንም ሆነ ፓርትርያርክነት። እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን በሙሉ ልብ
አባት የምንለው፤ እርሱም በእኩል ዓይን ልጆቼ የሚለን የመንጋ መሪ እንፈልጋለን።
በየብዙኃን መገናኛውና ማኅበራዊ መድረኮች የሚጥላላ፤ በየሄደበት በዚህችዉ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዓይንህ ላፈር እየተባለ የሚዘበትበት፣ የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ የሆነ አባት
እንዲኖረንም አንመኝም። ለዚህም ነዉ በአባቶች መካከል እርቅ ወርዶ እኔ የአጵሎስ፣ እኔ የጳውሎስ፤ እኔ የኬፋ በሚል የተበታተኑት የአንዲት እናት ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ጌታችን
«እረኛውም አንድ መንጋውም አንድ» እንዳለ በአንድ ጥላ ሥር አሰባስቡ የሚል ጥሪያችንን የምናስተላልፈው።
ብፁዓን አባቶቻችን፤ ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ውሳኔ በእናንተ እጅ ላይ ይገኛል። በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በጀኔቫው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተናገሩትን
እኛም እንድገመውና ስለ እውነት ፍርድ ካልተሰጠ « እግዚአብሔር እና ታሪክ ይፈርዳሉ። » ለውድቀቷም ሆነ ለልማቷ ከእናንተ በፊት የሚወቀስም ሆነ የሚወደስ አይኖርም። በቤተ
ክርስቲያኒቱ አንድነት ብሎም በምእመናን ኅብረት ከእናንተ በላይ የሚጠቀምና የሚከበር አይገኝም። ስለዚህም አሁንም ጥሪያችን ከእናንተ ላይ አትኩሯል። የተሸከማችሁት ኃላፊነት
የምትገኙበትንም መስቀለኛ መንገድ ከእኛ ከትናንሾቹ ልጆቻችሁ በተሻለ መንፈሳዊ ዓይን እናንተ ታዩታላችሁ ብለንም እናምናለን። ቀደምት የሃይማኖት አባቶቻችሁ አባቶቻችን እንኳን
የፓትርያርክነት ሥልጣን ቀርቶ የአንድ ገዳም አለያም ማኅበረ መነኮሳት አበምኔትነት ላለመቀበል ያደርጉት የነበርነዉን ሽሽት ከእኛ በላይ እናንተ ታዉቁታላችሁ። ስለ ትኅትናም ይሁን
ኃላፊነቱን በመፍራት እምቢታቸዉ ጠንቶ ሲያስቸግሩም በግንድ እስከመታሰር እንደሚደርሱም ይዘነጋል ብለን አናስብም።
በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የተጀመረዉ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ዝግጅት ከፍጻሜ ሳይደርስ፤ ባለፉት ፓትርያርክ ዘመነ ፕትርክና ተጀምሮ የነበረውና አሁንም በሂደት ላይ
ያለው የእርቀሰላም ጉዳይ እልባት ሳያገኝ የሚደረገውስ የፓርትርያርክ ምርጫ ጥቅሙ ለማን ነዉ? ተሰያሚዉ ፓትርያርክ እኮ በሙሉ ልቡ የሚቀበሉት ምእመናን ያስፈልጉታል። ለዚህም ነዉ
ለአባቶቻችን ስጋታችንን እንድናሰማ የተገደድነዉ፤
ዘወትር የምናከብራችሁ ብፁዓን አባቶቻችን፣
ጭንቀታችን ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ጸንቶ እንዲኖር ነውና ይህንኑ ጭንቀታችንን በሚከተሉት ነጥቦች ስናጠቃልል ብፁዓን አባቶቻችንም ለዚህ ጭንቀታችን ከፍተኛ ትኩረት
እንደምትሰጡት ሙሉ ተስፋ በማድረግ ነው።
ነ ጥ ቦ ቹ ም፦
1ኛ፤ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በመከፋፈል ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰዉ የጉዳት ጠባሳ እንዲሽር አባታዊ ብሎም መንፈሳዊ ኃላፊነታችሁን ለመወጣት ከሁሉም በላይ የቤተ
ክርስቲያናችንን አንድነት እንድታስጠብቁልን እንጠይቃለን፤
2ኛ፤ ከምንም በላይ የተሰጣችሁን ሃይማኖታዊ ግዴታ በማስተዋል እርቀሰላሙ ሳይቋጭና የቤተ ክርስቲያን አንድነት ሳይመለስ ወደ ፓትርያርክ ምርጫ የሚደረገዉን ዝግጅት እንድትገቱ
በትኅትና እንጠይቃለን፤
3ኛ፤ የመንፈሳዊ መሪ አባት ምርጫ ጉዳይ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሃይማኖት አባቶችና እንዲሁም የምእመናን ጉዳይ መሆኑን ከእኛ በላይ እናንተ ታዉቁታላችሁ። ስለሆነም ከቤተ
ክርስቲያኒቱ ቀኖና ውጭ የሚደረግ ጫና ካለ ይህን የመቋቋም መንፈሳዊ ጽናት እንድታሳዩ እንጠይቃለን፤
4ኛ፤ ከዓለም ዙሪያ የሚቀርበው የካህናትና የምእመናን ተማኅፅኖ ሰሚ አጥቶ ሢመተ ፓትርያርክ የሚፈጸም ከሆነ እንደ ደንቀዙ፣ እንደ ደብረ ታቦሩና እንደ ቦሩ ሜዳ በጉባኤ ለሊቃውንቱ
የመከራከሪያ ዕድል ተሰጥቶ የመጨረሻ ውሣኔ ያገኝ ዘንድ እናሳስባለን።
5ኛ፤ ለእኛ ለልጆቻችሁ ያልታየ፥ ለእናንተ ለአባቶቻችን ብቻ የታዬ ካለ፥ ከሢመተ ፓትርያርክ አስቀድሞ በዓለም ዙሪያ ተበትና ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ሁኔታውን የሚያስረዳ ግብረ ኃይል
ከመንበረ ፓትርያርክ ቢልካልን።
የጀርመን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን የተማኅጽኖ ደብዳቤ አቀረቡ |
6ኛ፤ በተራ ቁጥር አምስት የተጠቀሰውን ለማድረግ ከወጭ አንጻር የማይቻል ሆኖ ከተገኘ በውጭ የምንገኝ ሊቃውንት፣ካህናትና ዲያቆናት በያለንበት ሀገረ ስብከት ባሉት ብፁዓን አባቶቻችን
መሪነት ጉባኤ እንድናካሂድ ዕድሉ ቢሰጠን።
አንዲት ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በተመሠረተችበት የክርስቶስ ደም ጸንታ እንደምንትኖር እናምናለን።
ልዑል እግዚአብሔር አባቶችን ከፈተና፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመከፋፈልና ምእመናንንም ከመበታተን ይሰውርልን።
«እረኛውም አንድ መንጋውም አንድ» ይሁንበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የጀርመን ሀገረ ስብከት ካህናት እና ምእመናን