ሪቻርድ ኒክሰን 37ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው
ተመርጠው መንፈቅ ሳይሞላቸው ከአፍሪካ ሊጎበኛቸው
የሚመጣ አንድ መሪ እንዳለ ሰሙ። መሪው ታላቁ
የአፍሪካ አባት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ነበሩ።ለግርማዊነታቸው ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋራ
መገናኘት የተለመደ ቢሆንም የአሁኑ ጉብኝታቸው አጀንዳ
ግን ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን ይዟል:: ንጉሡ እድሜያቸው
እየገፋ ሲመጣ በተለይም ኮሚዩኒዝም በ1960ዎቹ
እየተንሰራፋ ከመምጣቱ ጋራ ተደማምሮ ወንበራቸውን
በዝግታ የሚሸረሽሩ ስጋቶች በረከቱ። ጃንሆይ ለወዳጅ
አገር አሜሪካ የልባቸውን ሊነግሩ ባሕር መሻገርን ያቀዱት
ያን ጊዜ ነው።የሶማልያ ኢትዮጵያን ለመውረር ማሴር፥
የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ሀገራቸው
በሶቭዬት ሕብረት ተጽእኖ እና ቁጥጥር ስር ለመውደቅ መቃረቧ፥ ኤርትራን የመገንጠል እንቅስቃሴ እና ጎረቤት እንዲሁም
ሌሎች የእስላም ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ማነጣጠራቸው አክራሪነትን እያስፋፉ መሆናቸው ኃይለ ሥላሴን እንቅልፍ ያሳጡ
ራስ ምታቶች ሆኑ።
እናም ወደ ዋሽንግተን አቅንተው መፍትሔ ለመሻት ወሰኑ አሜሪካንም ለጉብኝቱ ይሁንታ ሰጥታ ቀን ተቆረጠ ይሁን እንጂ
የፕሬዝዳንት ኒክሰን አስተዳደር የደኅንነት አማካሪ የነበሩት ሔንሪ ኪሲንጀር ለንጉሡ የጉብኝት ምክንያት ቁብ ሳይሰጡ
ለአለቃቸው ቀጣዩን የምክር ማስታወሻ ጻፉ።
=================================================================
ከ:ሔንሪ ኪሲንጀር
ጉዳዩ:ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋራ ስለመገናኘት
ማክሰኞ july 8, 1969, 10:30a.m.
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የቅርብ ወዳጃችን ናት በዚህ ጉብኝት ዋናው ዓላማችን
ሀ.አዲሱ አስተዳደር የነበረውን መልካም ግንኙነት እንደሚቀጥል ማሳየት
ለ.ግርማዊነታቸውን እንደ የምዕራቡ ዓለም አፍቃሬ መሪ እና በአፍሪካ ብጥብጦች ጦርነቶችን ሲከሰቱ ሰላም ፈጣሪ
አድርገን ክብር እንሰጣቸዋለን።
ይኽን ስናደርግ ዋና ችግር የሚሆንብን ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ደኅንነት ስጋትን አጋነው መመልከታቸው ነው:: ንጉሡ
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር መሣርያ ፍላጎታቸው ቢንርም አሁን ካለን የወታደራዊ አቅም እጥረት እና ለእርሳቸው ስጋት ካለን
ግምት አንጻር ጥያቄያቸውን ማርካት አንችልም።በተለይም ለወታደራዊ አቅም ስጋታቸው እገዛ መሻታቸው እኛ መርዳት
ከምንቸለው እና አሜሪካ በሀገሪቷ ላይ ካላት ፍላጎት በተጨማሪ ለኢትዮጵያ መረጋጋት ወሳኝ ከሆነው የኢኮኖሚ ልማት
ትኩረት ግርማዊነታቸውን ያስቀይሳቸዋል።
ግርማዊነታቸው
ግርማዊነታቸው በ76 ዓመታቸው፥ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በንግሥና ተቀምጠው ራሳቸውን የሚመለከቱት
የዘመናዊው ዓለም ስልጣኔ ታሪክ ማማ አድርገው ነው። በአፍሪካ ውስጥ በአንጋፋ መሪነት መታወቃቸውን ብቻ ሳይሆን
ከአህጉር ባለፈ በዓለም ጉዳዮች ላይም ስኬታማ እና አዋቂ እንደሆኑ ያስባሉ። መራሩ የጦርነት ወቅት ስደታቸው ሰሚ
ከማጣታቸው እና ኮሚኒስቶች አቤቱታቸውን በማጣጣላቸው ምክንያት ውጫዊ ገጽታቸው የተቀረጸው ጣሊያን
በ1930ዎቹ ኢትዮጵያ ላይ በፈጸመችው ወረራ እርሳቸው ሊግ ኦፎ ኔሽን ስብሰባ ላይ ባደረጉት አስደማሚ ንግግራቸው
ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ዙርያዋን በከበቧት ሙስሊሞች ስር መውደቅ የክርስቲያኗ ኢትዮጵያ የተለመደ ፍርሃት ነው። ሶቭዬት
ሕብረት ለጎረቤት ሶማሊያ፥ ሱዳን እና የመን እርዳታ መስጠቷን አጉልተው ያዩት አጼው ከተፈጠረባቸው የተጠቂነት
ስሜት የመነጨ ነው። ይኼም ንጉሡ አሜሪካ ኢትዮጵያን ኮሚስት ሙስሊሞችን የመከላከያ አጥር አድርጋ እንድትጠቀም
ግላጎት አድሮባቸዋል።
እነዚህ እይታዎች እና ሌሎቹም የመጡት ንጉሡ ላሳለፉት ፈታኝ የሕይወት ልምድ ትኩረት መስጠታቸው እና ንጉሣዊው
ስርዓት የፈጠረባቸው ስጉነት ጭምር ነው። ከዚህ በፊት ባገኘሃቸው ወቅት እንደተገነዘብከው ከጥልቅ ክህሎታቸው የተነሳ
እሳቤያቸውን ለማወቅ የተላበሱት እርጋታ እና ጸጥታ የሰፈነበት ስብዕናቸው አሳች እና ለማወቅ አዳጋች ያደርገዋል።
የኢትዮጵያየሀገርውስጥሁኔታእናየወጭፖሊሲ
ግርማዊነታቸው በሀገር ውስጥ ልክ እንደአብዛኛዎቹ ዘመናዊ የዘውድ ስርዓቶች በአሠራራቸው ግራ መጋባት ውስጥ
ወድቀዋል። መንግስታቸውን የገነቡት በፊውዳል ርዝራዞች እና በሕብረተሰቡ ውስጥ በማሕበራዊ ፥ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ
ላይ ተጽእኖ በሚያሳራፉ ከተሜ ከበርቴዎች ነው:- ሁሉም ሀገሩን ከውጭ አደጋ የሚታደግ ጠንካራ ሕዝብ በሚል
ታምኖባቸው። አሁን እነዚያ አካሄዶች ታላቅ የፖለቲካ ንቅናቄ ፍጥሮባችው አገኙት፤ በተለይም ወጣቱ እርሳቸው
ሊያቆዩት እና ላይቀይሩት ክችች ያሉበትን ፈላጭ ቆራጭ ኃይል ለመጣል ተነሳ።
በዚህም ምክንያት በቅርቡ በአዲስ አበባ በኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተሰቀሰው የተማሪዎች አመፅ እና
ግርማዊነታቸው ቢሞቱ ሊፈጠር የሚቸለው የፖለቲካ ምስቅልቅል እየጎለበተ የመጣ እኛም የምንጋራው ስጋት ነው።
ንጉሡ በሕይወት እያሉ መሠረታዊ የመንግስት ለውጥ ለማምጣት ምናልባት አይቻልም ነገር ግን ለመሠረታዊ የኢኮኖሚ
ልማት መፋጠን ተገቢውን አቅም ማዋል ድንገት ሊገነፍሉ ከሚችሉ ኃይሎች እና ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ቁጣ ማመለጫ
ሊሆን ይችላል በዚህ ረገድ ባለፈው የካቲት ወጣቶችን ወደካቢኔያቸው በማምጣት ቁልፍ የኢኮኖሚ ኃላፊነቶችን
በመስጠት መልካም እርምጃ ወስደዋል
እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በእቅድ በሚመጣው ለውጥ እና በቱግታው መካከል ሆነው መፍትሔ ሊያመጡ ይችላሉ።
ባለፉት አስርት ዓመታት በኢራን ሻህ እና በለውጥ አራማጆቹ ላይ በተተገበረው ዘዴ የስኬት ድርሻ አለን። የኢትዮጵያ
ችግር እልባት ያገኛል ወይ የሚለው ጥያቄ ክፍት እንደሆነ ይቆያል።
ዘመናዊነት ንጉሣዊ አገዛዝን የማይቻል ሊያደርግ ቢችልም ዘመናዊ አለማድረግ ደግሞ አመጽን ይብሱን ማገንፈሉ
አይቀርም።ከዚህ የመሐል ሀገር አለመረጋጋት በላይ የግርማዊነታቸው አፋጣኝ ችግር የኤርትራ ነጻነት ግንባር አመጻቸውን
መቀጠላቸው በኢትዮጵያ ሰሜን ምስራቅ ጥግ በወጭ ኃይል የሚታገዝ የሙስሊሞች እንቅስቃሴ እንዳለ ያሳያል። ግንባሩ
በአክራሪ ዐረብ መንግስታት መታጠቁ አደጋውን ያወሳስበዋል። የኢትዮጵያ ጦር የወሰደው የበቀል እርምጃ ደግሞ
አማጺያኑ በኤርትራ ሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትን እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።
የኢትዮጵያ ጦር አማጽያኑ ዋና ግዛት እንዳይቆጣጠሩ የመከላከል አቅም ቢኖረውም አመጹ አሳሳቢ ከመሆኑ በተጨማሪ
ጠቃሚ ግብአቶችን ሊያመናምን ይችላል። የአመጹ ውጤት የሚወሰነው ቀይ ባሕርን አቋርጦ ከየመን እና በተለይ ከኤደን
(ደቡብ የመን) በሚመጣው እርዳታ መጠን ነው።
ከግራ ዘመሙ የሱዳን መንግስት ለግንባሩ የሚሰጠው ከፍትኛ እገዛ ኢትዮጵያውያኖችን አስፈርቷቸዋል። በቅርቡ በኃይለ
ሥላሴ እና በሶማልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤጋል መካከል ግጭትን የማርገብ ስምምነት ቢፈጠርም በደቡባዊ ድንበር
አካባቢ ሶማሌዎች የኢትዮጵያ መሬት ይገባኛል የሚል አዝማሚያ እንዳላቸው ይጠረጥራሉ። በርግጥ ሶቭዬት እና ከቀይ
ባሕር ባሻገር ያሉ ዐረብ መንግስታት እርዳታ እና ተጽእኖ ሶማልያ መሬቷን ነጻ እንድታደርግ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ
ፖሊሲ ላይ ጫና አርፎበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኤጋል ወደ ውስጥ የሚመለከት ጠንካራ መሪ ከመሆኑ አንጻር
ከኢትዮጵያ ጋራ የተፈጸመው የድንበር ስምምነት ሊዘልቅ የሚችል ቢመስልም አዲሱ የሱዳን አክራሪ መንግስት እና
የሶቭዬት በደቡብ የመን መስፋፋት ንጉሡን አስፈርቷቸዋል።
ሆኖም ግን የኛ ምርጥ የደኅንነት ክፍል ሁኔታውን እንዲህ ይመለከተዋል:-
1. የሱዳን ግራ ዘመም መንግስት ለኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን በደቡብ ሱዳን አማጽያን አሉበት
2. ሶቭዬትም ብትሆን በደቡብ የመን ገና መሬት እያቀናች ነው:: ደቡብ የመን እና ሳዑዲ አረቢያ ሰላም የማውረዳቸው
ነገር ገና በሂደት ላይ በመሆኑ የሶቭዬት ሕብረትን አቅም ያሳንሰዋል።
በአጎራባች ሀገራት ላይ ካላቸው ስጋት ውጪ ግርማዊነታቸው ለዩናይትድ ኔሽን ሰላም አስጠባቂ እና ለአፍሪካ አንድነት
ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍ ቀጥለዋል። የአፍሪካ አንድነት መስራች ናቸው። የአፍሪካ ሕብረት እና የዩናይትድ ኔሽን
ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገዋል። ግርማዊነታቸው የአፍሪካ ሕብረትን ወክለው
የናይጄሪያን እርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመፍታት ያደረጉትን በርካታ ጥረት ማስታወስ ይኖርብሃል – ምንም እንኳ
ልፋታቸው ባይሳካም።
የዩናይትድስቴትስእናኢትዮጵያግንኙነት
በ1950ዎቹ መጀመርያ ንጉሡ በብልሀት ሕግን ተከትለው ከማንም ጋራ ሳያብሩ ለማንም ሳያደሉ በሚዛናዊነታቸው
በሦስተኛው ዓለም ሀገራት ክብርን ተቀዳጅተዋል በተግባርም ከአሜሪካ ጋራ የጠበቀ ልዩ ግንኙነት ነበራቸው። ለኢኮኖሚ
ልማታቸው እና የቡና ምርታቸው ዋና ገበያቸው ስንሆን ለኢትዮጵያ ጦር እና አየር ኃይል ዋነኛ የምግብ እና መሣርያ ረጂ
ነበርን።
በአሁኑ ወቅት ወደ 20 ሚልዮን የሚጠጋ የኢኮኖሚ ልገሳ እናድረጋለን የወታደራዊ እገዛ ደግሞ 12 ሚልዮን በየዓመቱ
እንረዳለን። ከአስመራ ወጣ ብሎ ባለው ቃኘው ጦር ሠፈር ትልቅ ጠቀሜታ አለን (ዝርዝሩ ይፋ አልተደረገም):: ይኽ
የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 1978 የሚዘልቅ ይሆናል። የቃኘው አቅጣጫ ለመባዛት ያስቸግራል ወይም በፍጹም
አይቻልም:: እንደዚያም ሆኖ ለኤርትራ አማጽያን ጥቃት የተጋለጠ ነው።
ማጠቃለያ
ግርማዊነታቸው እንደ አጋር ሀገር ወደዚህ የሚመጡት :-
1 የቀደመውን ግንኙነት ለማጥብቅ
2 በአፍሪካ ቀንድ ፈጣን አደጋ ሊያመጡ የሚችሉ ስጋቶችን ሊነግሩን እና
3 ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ነው
እኛ ደግሞ እንደጥንት ወዳጅነታቸው የጋበዝናችው
1 እርዳታችን ቀጣይ እንደሚሆን እናረጋግጥላቸዋልን
2 ኢኮኖሚውን ማሻሻሉን እንዲገፉበት አሳስባቸው
3 የጥሩ ግንኙነት “ዋጋን” አስረግጠህ ንገራቸው:: በቃኘው ጦር ሰፈር ላይ ያለንን ፍላጎት አስምርበት።
በአሁን ደረጃ የሚደረገው ወታደራዊ እርዳታ ልእርሳቸው ፍላጎት በቂ መሆኑንም አስረዳቸው።
በጉብዝና ዘመናቸው የነበራቸው ተጽእኖ እና ተደማጭነት አይከስምም ብለው ያሰቡት ጃንሆይ ጉልህ አጀንዳቸውን
በመያዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አቶ ከተማ ይፍሩን አስከትለው እና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ምናሴ
ኃይሌ በመታጀብ አሜርካንን ጎበኙ።
በማስታወሻው ላይ እንደሠፈረው ኪሲንጀር የጃንሆይን ስጋቶች አጣጥሎ ከወታደራዊ እርዳታ ይልቅ ኢኮኖሚው ላይ
እንዲተኮር ሪቻርድ ኒክሰንን መክሮ የጃንሆይን ስጋቶች አናናቀ። የሶቭዬት ሕብረት ኢትዮጵያን የመውረስ እንቅስቃሴ፥
የሶማልያ የወረራ እቅድ፥ ኤርትራን የመገንጠል አመጽ እና ጎረቤት እስላም ሀገራት እና ዐረቦች የክርስቲያን ደሴቷን
ኢትዮጵያ ለመሸርሸር የሚሸርቡት ሴራ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለአሜሪካ ግንዝቤ የራቁ ሆኑ።
ከዚያ ይልቅ በተዋቡ ቃላት ክባ፣ በጥሩ መስተንግዶ በዋይት ሐውስ አንሸርሽራ እና የኒክሰንን ቡችሎች አስጎብኝታ ዋናውን
ጉዳዩን በማድበስበስ ንጉሠ ነገሥቱን ሸኘች። ግርማዊነታቸው ከአሜሪካ የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ከመቀበል ሌላ
አማራጭ አልነበራቸውም ማለትም ኢኮኖሚ ላይ ማተኮር፣ የአፍሪካን ጉዳይ በንቃት መከታተል በተለይም በናይጄርያ
የተጋረጠውን ባያፍራን የመገንጠል ጦርነት እንዲያበቃ መፍትሔ እንዲፈልጉ ታዝዘው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
ነገር ግን ጊዜው ቢዘገይም የኃይለሥላሴ ‘ትንበያዎች’ መፈጸማቸው አልቀረም:: የዘውድ ስርዓት ተገረሰሰ፣ ሶማልያ እናት
ሀገር ኢትዮጵያን ወረረች፣ ሶቭዬት ሕብረት ሶሻሊዝምን አምጥታ አራግፋ የሀገሪቷን ጓዳ ጎድጓዳ በማወቅ ተጠቀመች፣
በዐረቦች የማያቋርጥ ወታደራዊ እርዳታ ሲረዳ የኖረው እና በወያኔ የታገዘው ሻዕቢያ ኤርትራን ገነጠለ።
ምን ቀረ? ጎረቤት እስላም ሀገራት እና ዐረቦች የራሳቸውን እስልምና በምስራቅ አፍሪካ ኃያሏ ኢትዮጵያ እና በሀገሪቱ
ፖለቲካ ውስጥ በማስፈን የክርስትናን የበላይነት ማክተም። ጊዜው ሩቅ አይመስልም::
ካሳሁን ይልማ የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ ሲሆን በCUNY (City of New York University) Graduate
School of journalism ጋዜጠኛነት እያጠና ይገኛል። በዚህ ኢሜል ማግኘትይቻላል:-
kassaddis@yahoo.com/kassahun.woldehanna@journalism.cuny.edu