አስገራሚው እና አነጋጋሪው ፍጻሜ-18 ጥይት ለምን?
ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም
ከጠዋቱ 2፡30 ገደማ ከካሳንቺስ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ እንደወትሮው የትራፊክ እንቅስቃሴ አጨናንቆታል፡፡ በተጨናነቀው በዚህ መንገድ ላይ ግን አንድ ሃችፓክ መኪና በአየር ላይ የሚበር በሚመስል ሁኔታ ይከንፋል፡፡ ከፊት ለፊቱ ባሉ መኪናዎች መንገድ የተዘጋበት የዚህ መኪና አሽከርካሪ ልክ ዮርዳኖስ ሆቴል ደጃፍ ጋር ሲደርስ ‹‹በአሳልፉኝ›› ምልክት በክላክስ አካባቢውን ያውከዋል፡፡
የክላክስ ድምፁ በተደጋጋሚ የተነፋላት ከፊት ለፊቱ ያለችው በተለምዶ ወያኔ ዲኤክስ መኪና አሽከርካሪ ክላክሱ ለእሷ የተነፋ አልመሰላትም ነበር፡፡ ወላጅ እናቷን ጭና ወደ ኦሎምፒያ አቅጣጫ መብራቱን ለመሻገር ጥረት ታደርግ የነበረችው አሽከርካሪ ከኋላዋ ያለውን ሰው ማንነት ለማረጋገጥ በመኪናዋ የጎን መስታወት ስፖኪዮ ስትመለከት በፍ/ቤት በፍቺ ወረቀት የተለየችው የሁለት ልጆቿ አባት መሆኑን ተመልክታለች፡፡
የቀድሞው ባለቤቷ የክላክስ ጩኸትና በተደጋጋሚ በእጅ ምልክት እንድትቆም የሚያሳያት ዛቻን ያላማራት ሚስት የመንገዱን መብራት በፍጥነት አቋርጣ ወደ ኦሎምፒያ ደንበል አቅጣጫ ሽቅብ መንዳት ትጀምራለች፡፡ ከኋላዋ እየተከታተላት ያለው አሽከርካሪም የመጨረሻ ፍጥነቱን ጨምሮ ይከተላታል፡፡ አጠገቧ ያሉት እናት ወ/ሮ ተናኜ ሀ/ማርያም ባሏ ምን እንደፈለገ ቆማ እንድታናግረው አለበለዚያም የፀጥታ ሀይሎች ወዳሉበት እንድትነዳ ሲጠይቋት የሁኔታውን አስፈሪነት በመረዳት ሁለተኛውን አማራጭ ነበር የመረጠችው፡፡ እናም ወደ ደንበል የሚወስደውን መንገድ በፍጥነት ነድታ አዲስ እየተሰራ ያለው አደባባይ ጋር ስትደርስ በአይኗ ግራና ቀኝ ፖሊሶችን ፍለጋ አማተረች፡፡
በወቅቱ በአካባቢው ላይ የትራፊክ ፖሊሶችና ሌሎች የፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ሠራተኞ ነበሩ፡፡ ሚስት አደባባዩን እንደተሻገረች ላፓራዚያን ካፌ ፊት ለፊት ከመድረሷ በፊት ከኋላ የሚከተላት የባሏ መኪና ሲጋልብ አጠገቧ ይደርሳል፡፡ አመጣጡ ያላማራት ሚስት መኪናዋን ካርቱም ሬስቶራንት ፊት ለፊት ባለበት ሁኔታ አቁማ በመውረድ ወደ ፀጥታ ሠራተኞች ለመሮጥ በመወሰን መኪናዋን ታቆማለች፡፡
የአደጋ መከላከያ ቀበቶዋን በፍጥነት ፈትታ ልትወርድ ስትል ግን መኪናው በበሯ አጠገብ ሲጢጥ ብሎ በማቆም አሽከርካሪው ወደ እሷ መጣ፡፡ በሯ በመኪናው መዘጋቱን የተመለከተችው ሚስት በሌላኛው የፊት በር በፍጥነት ወጥታ ለማምለጥ ጥረት እያደረገች ሳለ ረዥም ክላሺንኮቭ ጠመንጃውን እያቀባበለ ወደ እሷ የተጠጋው አሽከርካሪ በቀጥታ በመተኮስ በ18 ጥይት የሁለት ልጆቹን እናት ባለችበት ጣላት፡፡ ከተኮሳቸው ጥይቶች መሀከል ወላጅ እናቷን ሶስት ጥይት አግኝቷቸዋል፡፡ ሁኔታውን በስፍራው ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ የአይን እማኞች እንደገለፁት ከሆነ ያለምንም ንግግር ይህንን አስከፊ ድርጊት የፈፀመው ሰው በቀረው ጥይት ራሱን ለማጥፋት ወደርሱ ለመተኮስ ቢሞክርም ጠመንጃው ጥይቱን ጨርሶ ስለነበር መሞት አልቻለም፡፡ ይህ ከሁለት እስከ ሶስት ደቂቃ የፈጀውን ትዕይንት ለማስቆም ጊዜ ያጡት በአካባቢው የነበሩት የፀጥታ ሠራተኞች የድርጊቱን ፈፃሚ ዋና ተዋናይ በቁጥጥር ስር አድርገው ተጎጂዎቹን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ወዲያ ወዲህ ቢሉም ሚስት ወ/ሮ ፍሬህይወት ታደሠ ሰውነቷ ላይ ባረፉት 18 ጥይቶች ሳቢያ እስከወዲያኛው ያሸለበችው እዚያው መኪና ውስጥ ነበር፡፡
በስፍራው ሆኖ ድርጊቱን ሲከታተል የነበረውና ጫጫታው መሀል ሆኖ ስልክ የደወለልኝ ወዳጄ አርቲስት ሙሉቀን ተሾመ (የቴዲ ተሾመ ታናሽ ወንድም) የድርጊቱን ሁኔታ በሀይለቃል መግለፅ ቢችልም በወቅቱ ከዚህ የበለጠ ሁኔታውን ሊያብራራልኝ አልቻለም ነበር፡፡ የአልመንሱር ጄኔራል ትሬዲንግ ባለቤት አቶ መንሱር ጀማል ግን ድርጊቱን በሞባይሉ ፎቶ ማንሳት ችሎ ነበር፡፡
18 ጥይት ለምን?
የሁለት ልጆቹን እናት ወ/ሮ ፍሬህይወት ታደሰን በአስከፊ ሁኔታ በጥይት ደብድቦ በመግደል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው አቶ ወንድወሰን ይልማና ባለቤቱ ወ/ሮ ፍሬህይወት ትዳር መስርተው የሚኖሩ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ መስከረም 27 ቀን 1999 ዓ.ም የተፈፀመው የሁለቱ ጥንዶች የሠርግ ሥነ ሥርዓት እጅግ የደመቀ፣ የተለየና በከተማው በወቅቱ ትልቅ መነጋገሪያ የነበረ ሠርግ ነበር፡፡ (ስለ ሰርግ ሥርዓቱ ወደኋላ ላይ እመለስበታለሁ)
ወንድወሰንና ፍሬህይወት ከ1999 እስከ 2004 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ‹‹አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ›› እየተባባሉ በአንድ ጎጆ ውስጥ ኖረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም የአራት ዓመት ሴት ልጅና የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡ ወንድወሰን በተፈጥሮው ቁጡ፣ ግትርና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ባይ መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ከዚሁ ባህሪው ጋር በተያያዘም ከፍሬህይወት ጋር በተደጋጋሚ ይጋጫሉ፣ ሀሳቧን ስለሚጫናትም ለጠብ ይዳረጋሉ፡፡ አለፍ ሲልም ወንድወሰን ቡጢ እስከመሰናዘር ደርሶ በገላጋይ የተለያዩበት ጊዜ አለ፡፡
ከሁለተኛው ወንድ ልጅ መወለድ በኋላ አለመግባባታቸው እየተካረረ መምጣቱን የሚናገሩት ለጥንዶቹ ቅርበት ያላቸው ወገኖች የጠባቸው ትክክለኛ ምክንያት ይህ ነው ብለው ለመናገር ቢቸገሩም ፍሬህይወት ቀደም ሲል ትሰራበት ከነበረበት ክሊንተን ፋውንዴሽን መ/ቤት ለቃ የግል ሥራ ብሰራ ይሻለኛል ማለቷ ጠባቸውን ከቤተ ዘመድ ጉባኤና ሽማግሌዎች እጅ አውጥቶ ወደ ፍ/ቤት እንዲያመራ አድርጎታል ይላሉ፡፡
“የፍቺ ይፅደቅልኝ” ክስ መስርታ ወደ ፍ/ቤት ያመራችው ፍሬህይወት ‹‹ሁለት ልጆቼን ለማሳደግ አላንስም›› በማለት ፍቺው እንዲፀድቅላት ብቻ ወደ ፍ/ቤት ማምራቷ ወንድወሰንን አላስደሰተውም ሁለት ልጆች መውለዳቸውን የተረዳው ፍ/ቤትም ለልጆቻቸው ሲሉ አለመግባባታቸውን በሰላም እንዲፈቱ የማንሰላሰያ ጊዜ በተደጋጋሚ በመስጠት በቀጠሮ ቢያቆያቸውም መስማማት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ፍቺው በፍ/ቤት ሲፀድቅ ወንድወሰን ለጊዜው ደስተኛ መስሎ ታይቷል፡፡ የልጆቻቸውን ጉዳይ በተመለከተ ብይን የሰጠው ፍ/ቤቱ ‹‹ልጆቹ ከእናታቸው ጋር እንዲሆኑና በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ መጥቶ በመውሰድ አጫውቷቸው እንዲመልስ›› በተወሰነው መሠረት ይህንኑ ድርጊቱ ሰላማዊና ቤተሰባዊ በሆነ መልኩ ላለፈው አንድ ዓመት ወንድወሰን ተግብሮታል፡፡
የፍቼው እንግዳ
ሐምሌ 7 ቀን 2004 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ ከፍቼ የመጣ አንድ እንግዳ አዲሱ ገበያ አካባቢ ከፅዮን ሆቴል በታች ባለ አንድ ካፌ በረንዳ ላይ
በጥቁር ላስቲክ የተጠቀለለ ዕቃ ጀርባው ስር ሸጉጦ አስር ጊዜ ሰዓቱን ይመለከታል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ የአሁኑ ተጠርጣሪ ወንድወሰን ካፌው በር ላይ መኪናውን በማቆም ወደ ግለሰቡ ስልክ ይደውላል፡፡ ስልኩ በካፌው በረንዳ ላይ ወዳለው ሰው ሲጠራና ስልኩ ሲነሳ በአካል የማይተዋወቁት ተቀጣጣሪዎች ይተያያሉ፡፡ ወዲያው ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ እንግዳው ዕቃውን ይዞ ወንድወሰን መኪና ውስጥ መግባታቸውን ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ ምንጮች ይናገራሉ፡፡
መኪናው ውስጥ የገቡት ወንድወሰንና የፍቼው ሰው ጥቂት ደቂቃዎች ከተነጋገሩ በኋላ ‹‹ሌባ በተደጋጋሚ ግቢህ ውስጥ እየገባ እንዳስቸገረህ የነገረኝ ጓደኛዬ ስልክህን ሰጥቶኝ ደውልለት ስላለኝ ነው የመጣሁት›› አለው የፍቼው ሰው፡፡ ‹‹ዕቃውስ?›› የወንድወሰን ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ይዤዋለሁ›› በማለት በጥቁር ላስቲክ የተጠቀለለውን ክላሽንኮቭ አውጥቶ ሰጠው፡፡
ስጋት ጥርጣሬና ተስፋ በወንድወሰን ፊት ላይ ይነበብ ነበር ይላሉ ምንጮቻችን፡፡ ወንድወሰን ጊዜ
ሠርጋቸው
ሳያጠፋ በደላላው በኩል የተነገረውን 25 ሺህ ብር ከመኪናው የኋላ ወንበር ስር አንስቶ ለፍቼው ሰው ሰጠው፡፡ የፍቼው ሰው ብሩን መቁጠር ሳያስፈልገው ገለጥ አድርጎ ከተመለከተ በኋላ ከመኪናው ወረደ፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ ሌባ ግቢዬ እየገባ አስቸገረኝ›› ያለው ወንድወሰን መሳሪያውን ይዞ በግቢ ሌባ የመሰላት የልጆቹ እናት ላይ ለመሞከር የሚያስችለውን አመቺ ጊዜና ቦታ እያንሰላሰለ ቁል ቁል ወደ ፒያሳ አቅጣጫ ተፈተለከ፡፡
መስከረም 27 ቀን 1999 ዓ.ም በተከናወነው የአቶ ወንድወሰን ይልማና የወ/ሮ ፍሬህይወት
ታደሰ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ቁም ነገር መፅሔት የመገኘት ዕድል ገጥሟት ነበር፡፡ በወቅቱ ለ3 ዓመታት ያህል የዘለቀውን የፍቅር ግንኙነታቸውን በጋብቻ ለመቋጨት የወጠኑት ወንድወሰንና ፍሬህይወት ወደ ትዳር ሲገቡ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጠርተው የደስታቸው ተካፋይ የሚያደርጉበትን የሠርግ ዝግጅት በምን መልኩ እና እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው ሲያወጡና ሲያወርዱ ነበር የከረሙት፡፡ በተለይ ወንድወሰን ጋብቻው እስከዛሬ ድረስ ከተደረጉት ሠርጎች ሁሉ ለየት ያለ እንዲሆን አጥብቆ ነው ያሰበበት ‹‹ፍላጎቴ ከሌሎች ሰዎች ለየት ብዬ እንድታይ አይደለም›› የሚለው ወንድወሰን ‹‹ይልቁንም የአሁኑ ትውልድ ራሱን ሆኖ በራሱ ባህልና ትውፊት የመድመቅ ችግር ስለሚታይበት ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግን የተከተለ ሠርግ በማድረግ ራሴን ሆኜ ለመገኘት ነው›› ብሏል በወቅቱ ለቁም ነገር መፅሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ፡፡
ወንድወሰን በከተማችን ከታዩት የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ሁሉ የተለየ ከውጥኑ ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግን የተከተለ ታሪካዊ አሻራ ያለው ሠርግ ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ፍሬህይወት ምንም እንኳን መጨረሻ ላይ በሃሳቡ ተስማምታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ብትጀምርም ‹‹ሠርጋችን ምንም አይነት ዘመናዊ ነገር የማይገባበት በባህል ተጀምሮ በባህል የሚያልቅ መሆን አለበት›› በሚለው የወንድወሰን ሀሳብ አልተስማማችም ነበር፡፡ ከውይይት ይልቅ የወሳኝነት ባህሪ ያለው ወንድወሰን ግን ከስምምነታቸው በፊት አንዳንድ ወሳኝ ነገሮችን ይዞ የሰርግ ስነ ሥርዓቱን ጀምሮ ነበር፡፡
የጥሪ ካርድ
በዚሁ መሠረት ወንድወሰን ለዘመን አመጣሽ የሠርግ ዝግጅቶች ቦታ አልሰጠም፡፡ የሠርግ ካርዱን በማተሚያ ቤት ከማሳተም ይልቅ በብራና ላይ በቁም ፅሁፍ ተፃፈ፡፡ ይህንኑ የጥሪ ካርድ በፖስታ ውስጥ ጨምሮ ለእድምተኞች ከመስጠት ይልቅ ብራናው ተጠቅልሎ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው ጠፈር ሸብ የተደረገ ነበር፡፡ የጥሪ ካርዱን በብራና ላይ ለማፃፍ ሀሳቡን ያፈለቀው ወንድወሰን ቢሆንም ዲዛይኑን በመስራት በኩል የኮምፒውተር እውቀት ያላት ባለቤቱ አግዛዋለች፡፡
አልባሳት
‹‹ሠርግ ያለዘመናዊ ቬሎ የማይታሰብ ሊመስለን ይችላል›› የሚለው ወንድወሰን የባለቤቱን መሞሸሪያ ቬሎ በሀገር ውስጥ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሰራ አድርጓል፡፡ የባለቤቱ ልብስ ብቻ ሳይሆን የእሱም ሆነ የወንዶቹና የሴቶቹ ሚዜዎች አልባሳትና መጫሚያ ሁሉ የእጅ ጥበብ ውጤቶች ነው የተደረጉት፡፡
ጌጣጌጦች
የመዋቢያ ጌጣጌጦችም በተቻለ መጠን ባህላዊ እንዲሆኑ ተወጥኗል፡፡ የሙሽሪት የእጅና የአንገት፣ የጆሮና በፀጉር ላይ የሚሰኩት ጌጣጌጦች በሙሉ ጨሌዎችና ከቀንድ የተሰሩ ነበሩ፡፡ የሙሽሮቹ መቀመጫ ወንበር ከጠፈር የተሰራ፣ የእግራቸው ማረፊያም ምንጣፍ አጎዛ፣ በዙሪያቸው ያለው ዲኮር በሙሉ በሀገር ባህል ጥበብ የተሰራ ነበር፡
ምግብና መጠጥ
ከላይ ከቀረበው እቅድ አንፃር ምግብ ባህላዊ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ሠርጉ የፈረንጅ ምግቦች እንዳይቀርቡበት ብቻ ሳይሆን አቀራረቡም ባህላዊ እንዲሆን ተፈልጓል፡፡ በዚሁ መሰረት የክትፎ አይነቶች ከነማባያቸው አይብና ጎመን ጋር ሲቀርቡ መመገቢያ ዕቃዎቹም ከቀንድና ከሸክላ የተሰሩ ሆነዋል፡፡ መጠጡም ውስኪንና ሻምፓኝን በማስወገድ ጠላና ብርዝ ነበር በብርሌ የቀረበው፡፡ በኬክ ፋንታም ሻኛ ድፎ ተቆርሷል፡፡
አጃቢዎች
ይህ ሁሉ ባህላዊ ነገር ተዘጋጅቶ አጃቢዎች ሙሽሮቹን በመርቸዲስ እንደማይሄዱ መገመት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ወንድወሰን አስቀድሞ በባልደራስ ስር ያሉ የቤተ መንግስት ፈረሶችን ከነሠረገላቸው ለመከራየት ተነጋግሮ ስለነበር በዕለቱ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሽር ብለዋል፡፡ ከሙሽሮቹ ፊት ለፊት ነጋሪት የሚጎስሙ ወጣቶች በጥንታዊው የባህል አልበሳት ደምቀው ነበር፡፡ ከፈረሰኞቹ ፊት ደግሞ እምቢልታ የሚነፉ ሻምላና ምንሽር የታጠቁ አባቶች፣ በርኖስ የደረቡ ጭንቅላታቸው ላይ አንፋሮ አድርገው ዝናር በታጠቁ ወጣቶች ታጅበው ነበር ከአራት ኪሎ ወደ ካሳንቺስ ሲያመሩም በየመንገዱ ያለ ህዝብ ግራና ቀኝ ቆሞ በአድናቆት አጅቧቸዋል፡፡
እንግዶች
ሁሉም ነገር ባህላዊ በሆነበት በዚህ ሠርግ ስነ ስርዓት ላይም እንግዶች የራሳቸውን የባህል አልባሳት ለብሰው እንዲገኙ ነበር የወንድወሰን ፍላጎት ‹‹የባህል ልብስ ያልለበሰ እድምተኛ ወደ ሠርጉ አዳራሽ መግባት የለበትም›› የሚል አቋም ይዞ የነበረው ወንድወሰን ዝግጅቱ ሠርግ በመሆኑ እድምተኞችን ማስገደድ ተገቢ እንዳልሆነ በሙሽሪት ቤተሰቦች በኩል ተቃውሞ እስኪመጣበት ድረስ በአቋሙ ገፍቶበት ነበር፡፡ ያም ሆኖ እድምተኞች የፈለጉትን ልብስ ለብሰው እንዲመጡ ወንድወሰን በሀሳቡ ቢስማማም የጥሪ ካርዱን ሲልክ ግን የባህል ልብስ ለብሰው እንዲመጡ የሚጠይቅ መልዕክት አብሮ ከመላክ አልቦዘነም ነበር፡፡ በዚሁ መሠረትም ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው በተጨማሪ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ውስጥ የሆኑ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣልያንና የጃፓን የባህል አታሼዎች የሠርግ ሥነ ሥርዓቱን ተከታትለዋል፡፡
የሠርግ ሥነ ሥርዓትን በክብር እንግዳ ፊት ማከናወን የተለመደ አይደለም፡፡ ወንድወሰን ግን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑትን ወ/ሮ ታደለች ዳለቾን የባህል ልብስ እንዲለብሱ ከሚያሳስብ መልዕክት ጋር ጋብዟቸው ስለነበር በሀገር ባህል ልብስ ደምቀው በሠርጉ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ተመልክተናል፡፡
ወንድወሰን ማነው?
አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው የ43 ዓመቱ ወንድወሰን ይልማ በቤተሰብ ግጭት ሳቢያ ከወላጆቹ የተለየው ገና የ7 ዓመት ልጅ ሆኖ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያም ክፍለሀገር ዘመዶቹ ጋር ነው ለረዥም ዓመታት የኖረው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የቴክኒክና ሙያ የተማረው ወንድወሰን የራሱን አነስተኛ የብሎኬትና የሸክላ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ከፍቶ ትዳር እስከመሰረተበት ጊዜ ድረስ ድርጅቱን በበላይነት መርቷል፡፡
ፍሬህይወትስ?
ያለፈው መስከረም 2 ቀን 2005 ዓ.ም የ29ኛ ዓመት የልደት በዓሏን ያከበረችው ፍሬህይወት ተወልዳ ያደገችው እዚሁ አዲስ አበባ ፤ነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በጀኔራል ዊንጌት ት/ቤት ያጠናቀቀችው ፍሬህይወት ከዊንጌት የ10 ሲደመር 3 ዲፕሎማ ተቀብላለች፡፡ ከዚያም በሲፒዩ ኮሌጅ እየተማረች የማትሪክ ውጤቷ ስለተሻሻለላት በማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ ገብታ በማኔጅመነት ኢንፎርሜሽን ሲስተም በዲግሪ ተመርቃለች፡፡
ፍሬህይወት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን፣ ኋላም በብራዘርስ ፉድ ኮምፕሌክስና በሰላም የጉዞ ወኪል ውስጥ በፀሐፊነትና በዲዛይነርነት የሰራች ሲሆን ለሞቷ ምክንያት የሆነውን የግል ሱቋን ከመክፈቷ በፊት በክሊንተን ፋውንዴሽን ውስጥ አገልግላለች፡፡
እንዴት ተዋወቁ?
ትውውቃቸው በአጋጣሚ ነው፡፡ አጋጣሚውን የፈጠረው ደግሞ ወንድወሰን ነው፡፡ ወቅቱ ደግሞ 1996 ዓ.ም፤ ወንድወሰን በግል የብሎኬትና የሸክላ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጎንበስ ቀና ሲል የወገብ ህመም ያጋጥመዋል፡፡ ህክምና ለማግኘት ደግሞ ቦሌ ድልድይ አካባቢ ወደሚገኘው ቦሌ ካይሮ ፕላስቲክ ክሊኒክ ያመራል፡፡
ገና ወደህንፃው የእንግዳ መቀበያ ሲገባ ከአንዲት ብስል ቀይ ቆንጆ ልጅ ላይ አይኑ ያርፋል፡፡ ልጅቱን ተከትሎ ሲሄድ ሊፍት ያለበት ቦታ ትቆማለች፤ ሊፍቱ ሲመጣና ስትገባ እሱም ይገባል፡፡ ክሊኒኩ ያለበትን ፎቅ ሲጠይቃት 6ኛ ፎቅ ላይ እንደሆነ በመንገር 2ኛ ፎቅ ላይ ጥላው ትወርዳለች፡፡
ወንድወሰን ክሊኒክ ገብቶ ካርድ አውጥቶ ታክሞ ከጨረሰ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤቱ አላመራም፡፡ ልጅቱን ፍለጋ ወደ 2ኛ ፎቅ እንጂ፡፡ ግን ልጅቱን በስምም ሆነ የምትሰራበትን መ/ቤት ባለማወቁ ወደ እንግዳ መቀበያው ወርዶ ለእንግዳ ተቀባዩ አድራሻውን እንድትሰጥለት አደራ ሰጥቶ ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ በህንፃው ውስጥ ካሉት መ/ቤቶች መሀከል በሰላም የጉዞ ወኪል ውስጥ የምትሰራው ፍሬህይወት የስልክ አድራሻው ከደረሳት ከቀናት በኋላ ስልክ ትደውልለታለች፡፡ ‹‹የመ/ቤቴ የሥራ ባህሪ ከብዙ ደንበኞች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ከደንበኞቻችን አንዱ ይሆናል ብዬ ነበር የደወልኩለት›› ብላለች በወቅቱ ለቁም ነገር መፅሄት በሰጠችው ቃለ ምልልስ፡፡ ወንድወሰን ግን ስትደውልለት ምን ሊላት እንደሚችል አስቀድሞ ተዘጋጅቶበት ስለነበር ተገናኝተው እንዲነጋገሩ በመጠየቅ ይቀጣጠራሉ፡፡ ተገናኝተው ሲነጋገሩ ይግባባሉ፤ ውሎ ሲያድር በፍቅር ይወድቃሉ፡፡
ሁሌም በንግግሩ መሀል የእግዚአብሔርን ስም ሳይጠራ ቆይቶ የማያውቀው ወንድወሰን ስለ እያንዳንዱ ነገር መተቸትና ከሥር መሰረቱ ጀምሮ ማብራራት የሚወድ ሰው ነው፡፡ ‹‹አፉ ጤፍ ይቆላል›› ይላሉ የቅርብ ጓደኞቹ የንግግር ችሎታውን ሲገልፁ፡፡ ወንድወሰን ከመደበኛ ሥራው ውጪ በሥነ መለኮት ትምህርት የተመረቀ ሲሆነስ ሁለቱም የፕሮቴስታን ሀይማኖት /ሙሉ ወንጌል?/ ተከታይ ናቸው፡፡
የአስገራሚው ሠርግ መጨረሻ
ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ በአህያ ከአጠና ጋር ተጭኖ የገባው መሳሪያ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ በወንድወሰን እጅ ሲፈታታና ሲገጣጠም፣ ሲወለወልና ሲሞከር ከርሟል፡፡ ከፍ/ቤቱ ውሳኔ በኋላ በተደጋጋሚ ‹‹የእገድልሻለሁ›› ዛቻ ያደርግባት የነበረችው ፍሬህይወት ጉዳዩን በቀላሉ ባለማየት ለቤተዘመድ ጉባኤና ለሽማግሌዎች ብታሳውቅም የዛቻውን እውነተኛነት ለማስረዳት ባለመቻሏ ተቀባይነት ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ ነገሩ እጅግ እየተደጋገመና እየበዛ ሲመጣ ግን ወደ ህግ ለመሄድ ተገዳለች፡፡ ‹‹ለህይወቴ ያሰጋኛል›› በማለትም ፖሊስ ጣቢያ ማስመዝገቧን ቤተሰቦቿ ይናገራሉ፡፡
የወንድወሰን ዛቻ ነፍስ ዘርቶ ከፍቼ ባገኘው ‹‹የሌባ መከላከያ መሣሪያ›› ሞራል አግኝቶ የሁለት ልጆቹን እናት ለመቅጠፍ ማሴር የጀመረው ግን ጥቅምት ከገባ ጀምሮ መሆኑን የሟች ቤተሰቦች ያስታውሳሉ፡፡ ዘወትር ቅዳሜ ቅዳሜ ከካሳንቺስ መናኽሪያ አካባቢ ከሚገኘው የወላጆቿ ቤት እየመጣ ልጆቿን ወስዶ በማዝናናት የሚመልሰው ወንድወሰን ጥቅምት ከገባ በኋላ ግን መጥቶ ልጆቹን አልወሰደም፡፡ በሁለተኛው ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን ጠዋት ግን ወደ መናኽሪያ ያመራው ልጆቹን ፍለጋ ሳይሆን እናታቸውን ፍለጋ ነበር ተብሏል፡፡
እናም ከጠዋቱ 2፡30 ገደማ ከቤት በመውጣት ደምበል አካባቢ ወደሚገኘው ሱቋ እናቷን ጭና ስታመራ ከኋላዋ መኪናውን አስነስቶ መከተል ጀመረ. . . . .የሆነውም ሆነ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment