Pages

Dec 8, 2012

ኢሳት ዜና:-የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፕሬዚዳንት፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮጵያ መንግስት ሕገ መንግስቱን እንዲያከብር፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ሕገ-መንግስታዊ መብቱ እንዲከበር እንዲታገል ጥሪ አደረጉ።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለሕዝብና ለመንግስት ጥሪ አደረጉ

ህዳር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፕሬዚዳንት፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮጵያ መንግስት ሕገ መንግስቱን እንዲያከብር፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ሕገ-መንግስታዊ መብቱ እንዲከበር እንዲታገል ጥሪ አደረጉ።

ዶ/ር ነጋሶ ዛሬ አርብ ህዳር 28 ቀን ከኢሳት ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባደረጉት ቃለምልልስ፤ ኢህአዴግ ከጥቂት አመታት ወዲህ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እያለ የሚጠራው ህዳር 29 ቀን፤ በዋንኛነት ሕገመንግስቱ የጸደቀበት ቀን እንደሆነ በማስታወስ፤ ኢህአዴግ ቆም ብሎ በማሰብ የህገ መንግስቱን የሰብአዊ መብት አንቀጾች እንዲያከብርና እንዲያስከብር አሳስበዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ሕገ መንግስቱ በሚረቀቅበትም ግዜ ይሁን በሚጸድቅበት ግዜ ስህተቶች እንደተሰሩ አስታውሰው፤ ህገ መንግስት የማይለወጥ የመጽሀፍ ቅዱስ ቃል ስላልሆነ፤ ኢህአዴግ ህገመንግስቱን እንዲያሻሽልም ጠይቀዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት፤ የገዢውን ፓርቲ የአምባገነንት ባህርይ በመተንተን፤ ገዢው ፓርቲ “ተገዶ እንጂ በልመናና በመለማመጥ በፈቃደኝነት በህዝብ የሚፈለገውን ለውጥ እንደማያመጣ” ገልጸው የጻፉትና ህዝቡም የተበታተነ ብሶቱንና ምሬቱን ወደአመጽና እምቢተኝነት መለወጥ እንዳልቻለ የተቹት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ሀሳባቸውን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ውይይት አብራርተዋል።

ከህዝቡ ምሬት ወደ አመጽ ያለማደግ ሁኔታ ጋር በተያያዘም ምክንያቱ የተለያዩ እንደሆነ ገልጸው፤ በተለይም ከምርጫ 97 በፊትም በሁዋላም ኢህአዴግ በህዝቡ ላይ ባደረሰው የጭካኔ ጥቃት ምክንያት በህዝቡ ላይ የፍርሀት ድባብ ሰፍኖ እንደሆነ ተናግረው፤ ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳይጠብቅ፤ መብቱን ለማስከበር መስራት አለበት ብለዋል።

ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለምልልስ በሬድዮ ፕሮግራማችና ላይ ይከታተሉት።

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate