Pages

Mar 31, 2013

ወ/ሮ አዜብ ተጨንቀዋል!

“ከሁሉም ነገር ጽድት ብለን እንታገል”

azebb mesfin

ሰሞኑንን በተጠናቀቀው የኢህአዴግ ጉባኤ አቶ መለስን አስመልክቶ ወ/ሮዋ የተናገሩት ንግግር በጭንቀት ውስጥ ስለመሆናቸው ማሳያ እንደሆነ የተናገሩት አብረዋቸው ባህር ዳር ስብሰባ የተቀመጡ የድርጅታቸው ኢህአዴግ “ባልደረቦቻቸው” ናቸው።
በጉባኤው ወቅት አቶ መለስ ዜናዊን በማወደስ የተዘጋጀው “ዝክረ – መውደስ” ታሪካዊ ሰነድ እንዲሆን ከመጽደቁ በፊት ወ/ሮ አዜብ በሰጡት አስተያየት “በፔሮል የሚከፈለው ብቸኛ መሪ መለስ ብቻ ነው” በማለት ራሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በፔሮል በሚከፈላቸው ገንዘብ ብቻ እንደማይኖሩ የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል።
መለስ ደመወዛቸው ስድስት ሺህ ብር እንደሆነ፣ ሁለት ሺህ ብር ሲቆረጥ አራት ሺህ እንደሚቀርና “ይህችኑ ገንዘብ” እየተቀበሉ ላገር ሲሰሩ ያለፉ መሪ መሆናቸውን ያወሱት ባለቤታቸው፣ ለመለስ ዝክረ-መወደስ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ይህ መካተት ይገባዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
“መለስ ጭንቅላቱን ይዞ ወደዚህች ዓለም መጣ፣ ለዚህች ዓለም፣ አገር፣ ምድር፣ የምታገለግል ሃሳብ አመነጨ” ያሉት ወ/ሮ አዜብ፣ ባለቤታቸው ግለኝነት ሳይፈታተናቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን በመርሳት፣ ላገራቸው የለፉና ድህነትን ሲዋጉ ኖረው ያለፉ መሪ መሆናቸው ሊረሳ እንደማይገባው አመልክተዋል። አያይዘውም ሊተኩ የሚችሉ መሪ እንዳልሆኑ በማሳሰብ ዝክረ-መወድሱ ከአቶ መለስ የሕይወት ጉዞ ብዙ ቁምነገሮችን የዘለለና ያልተሟላ ነው ብለውታል፡፡ እንዲሁም መለስ የኢትዮጵያ መሪም ብቻ ሳይሆኑ የአዲስ ራዕይ መጽሄት አዘጋጅ መሆናቸው አለመጠቆሙ አግባብ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ የተገኙ የድርጅት አባላት እርስ በርሳቸው ሲለዋወጡ የነበረውን የተከታተሉና በግልጽ ከስርዓቱ ባህርይ በመነሳት ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ እንዳሉት ወ/ሮ አዜብ የቀድሞው ስብዕናቸው አብሯቸው የለም። እንዲያውም በጭንቀት ውስጥ ያሉ ይመስላሉ ብለዋል።
በድርጅቱ አባላት ከላይ እስከታች የባለቤታቸውን ስልጣን ተገን በማድረግ በጣልቃ ገብነታቸውና ከፍተኛ የሚባል ንብረት በማካበት የሚታሙት ወ/ሮ አዜብ የባለቤታቸውን ስም በመደጋገም የሚያነሱት የሚታሙበትን ጉዳይ ለማስረሳት እንደሆነ እርስ በርስ በእረፍት ሰዓት ይወራ እንደነበር እነዚሁ ክፍሎች ተናግረዋል።
“ሴትየዋ በግልጽ ስለሚነሳባት ጉዳይ ለምን አትናገርም” በማለት የጠየቁ እንዳሉ፣ ከዚህም በላይ በድርጅቱ ውስጥ ነግሷል የሚባለው ሙስና በግልጽ ለምን አጀንዳ ሆኖ እንደማይቀርብ አባሉ ውስጥ ውስጡን ሲያወራ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። በትክክለኛው መንግድ ለመታደስና ለመጥራት የሙስና ጉዳይ የድርጅቱ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት አስተያየት የሰጡም አሉ።
ወ/ሮ አዜብ ይህ ገብቷቸው ይሁን አይሁን ስለ ባለቤታቸው ድህነት ሲናገሩ “እንደሚባለው ሳይሆን እኛ እንኮራበታለን” ማለታቸው ከሙስና ጋር በተያያዘ ስጋት ስለገባቸው የአባሉን ልብ ለማራራት እንደሆነ አድርገው የወሰዱትም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። በግልጽ ባያብራሩትም “እንደሚባለው” ብለው በመጥቀስ በይፋ እስከማስተባበል መድረሳቸው በባለቤታቸው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ራሳቸውም የተረዱት አይመስልም፡፡
አቶ መለስ ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ በሚያገኙት መድረክ ስለ ባለቤታቸው ድህነትና ያለ እረፍት ያለፉ መሪ በማድረግ በስፋት የሚናገሩት ወ/ሮ አዜብ፤ ባለቤታቸውን ዴሞክራት መሪ አድርገው ቢስሉም ሪፖርተር በፖለቲካ አምዱ ያስነበበው እውነተኛ ታሪክ የስጋታቸውና የፍርሃታቸው መነሻ እንደሚሆን ከግምት በላይ የሚናገሩ አሉ። ሪፖርተር ወ/ሮ አዜብን በስም ባይጠቅስም፣ “መሐንዲስ አልባው መተካካት” በሚል ርዕስ በጻፈው “(መለስ) በተለያዩ ጊዜያቶች የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ከፖለቲካ ጨዋታ ውጪ ማድረግ ቢችሉም፣ እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ ሥልጣን የግላቸው አልነበረም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ላይ ሆነው የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ሰውም አልነበሩም፡፡ በወቅቱ የሕወሓት መሰንጠቅን ተከትሎ የድርጅቱ ርዕዮተ ዓለም ቁንጮ (አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም) የወታደራዊ ስትራቴጂ ባለቤት (የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ)፣ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊው (የቀድሞ የትግራይ ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አስራት) እና ሌሎች የድርጅቱ ከ10 በላይ ከፍተኛ አመራሮች መወገድን አስከትሏል፡፡ የእነዚህ የድርጅቱ ወሳኝ ሰዎች መወገድን ተከትሎ በመንግሥትም ሆነ በፓርቲ ሥልጣናቸውን የተደላደለና ምንም የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሌላቸው ሰው መሆን የቻሉበት ጊዜ ነበር፡፡ የፈለጉትን ሕግ ማውጣት ያልፈለጉትን የመደቆስ ሥልጣኑም ጉልበቱም ነበራቸው” ሲል ሪፖርተር የጻፈላቸው አቶ መለስን ተገን በማድረግ ወ/ሮ አዜብ በሃብት፣ በጣልቃገብነት፣ በተለያዩ ውሳኔዎች፣ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው መቆየታቸው በርካታ ወዳጅ ያፈራላቸው ባለመሆኑ የስጋታቸው መጠን ሰፊና ጥልቅ እንደሆነ በስፋት አስተያየት እየተሰጠበት ነው።

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate