በዛን ወቅት ከነበሩት መካከል ዛሬ በእስር ላይ የምትገኘው ርዮት አለሙ፤ (እንደውም፤ እርሷን የተዋወቅኋትም የዛኔ ነበር መሰለኝ፤ አስታውሳለሁ ወደ መንፈሳዊነት የሚጠጋ አንድ ጽሁፍ አንብባልን ነበር፤ ጽሁፉ መንግስታችን መቅስፍትነቱን ትቶ በመንግስትነት እንዲቀጥል በዘዴ በዘዴ የሚመክር ነበር፡፡
ፕሮፍም ለርዮት አለሙ አስተያየት ሲሰጡ “መጽሀፍ ቅዱሱን ደህና አድርገሽ ጠጥተሸው የለም እንዴ…” ሲሏት አስታውሳለሁ፡፡ በዕለቱ ከነበሩት መካከል፤ ሌላ የእኔ ወዳጅ ደራሲ እና ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬም ነበር፡፡ የማይረሳኝ፤ በፕሮፍ ሁለንተናዊ ነገር ሲደነቅ ሲደነቅ ሲደነቅ ነበር፡፡ የፕሮፍን መንፈሳዊ እና አካላዊ ጥንካሬ አይቶ የማይደንቀው ማን አለ… ?
…ሌላ፤ እኔን ራሴን ወደ ፕሮፍ ቤት እንድሄድ የጋበዘኝ ወጣቱ ፖለቲከኛ አርዓያ ጌታቸው ነበር፡፡ የዛን ዕለት የልደት ዝግጅቱን ካዘጋጁት ዋነኛው እርሱ ነበር፡፡
ከአርአያ ጋር ሌላም ጊዜ እየተቀጣጠርን በተደጋጋሚ የፕሮፍን ምክር ኮምኩመናል፡፡ ሌሎችም በርካታ ወጣት ፀሀፊያን እና ፖለቲከኞች እንዲሁም መደበኛ ነዋሪዎች በፕሮፍ ልደት ላይ ተገኝተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ በልደታቸው ብቻ ሳይሆን ከልደታ እስከ ልደታ አዘውትረው ፕሮፍ ቤት የሚመላለሱ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ቤት የማይወጋ ጉዳይ የለም፡፡ በተለይ ግን ስለ ሀገር፣ ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ስለ ህዝቡ፣ ስለ ወቅታዊ ሁኔታዎች ስለ ወዘተ. ይወጋል ይወጋል ይወጋል… ይሄንን የለመደ ሰው ፒያሳ ከደረሰ ፕሮፍ ቤት ሂድ ሂድ ያሰኘዋል፡፡ ሄዶም ዩኒቨርስቲዎቻችን በአመታት የማያስጨብጡትን እውቀት ከፕሮፍ ቤት በአንድ ቀን ውስጥ ዘገን አድርጎ ይወጣል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ለዛች ሀገር በጣም የሚያስፈልጉ ሰው ናቸው፡፡ በተለይ ምክራቸውን የሚሰማ ሰምቶም ከልቡ የሚጽፈው ሰው ቢገኝ እንዴት መልካም ይሆን ነበር፡፡
በዛን ሰሞን ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ እና ውብሸት ታዬ መታሰራቸውን ሰምተን በድብርት ስሜት ፕሮፍ ቤት ሄደን ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ እነ ውብሸት ሲታሰሩ መንግስት “የቴሌ እና የመብራት ሃይል ተቋማትን ሊያፈርሱ ሲሉ ደርስኩባቸው” ሲል የሰጠው መግለጫ አስገርሞናል፡፡ ፕሮፌሰር ግን ይሄ የሚያሳየው መንግሰት ጨርቁን ጥሎ ማበዱን ነው ብለው ነገሩን…
እኛም መንግስታችን ከእብደቱ ይድን ዘንድ ፀሎት ጀመርን ግና ጭራሽ ባሰበት… እነ አቶ አንዷለም አራጌ እስክንድር ነጋ ጋሽ ደበበ ሳይቀር መታሰራቸውን ድጋሚ ሰማን… ይሄን ጊዜ ፕሮፍን አማከርናቸው… “መንግስት እንግዲህ የተነፈሰውን ሁሉ የሚያስር ከሆነ መፍትሄው ምንድነው…” አልናቸው… ፕሮፍም አሉን፤ “መፍትሄው አሁንም አሁንም መታሰር ነው! …ለውጥ ያለው እስር ውስጥ ነው!” አሉን፡፡ እውነት ብለዋል… እኛ አልሰማ ብለን ከሀገር ወጥተናል እንጂ ለውጡ ያለው እስር ቤት ውስጥ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አሁንም ሳይታክቱ እኛንም መንግስትንም እየመከሩ ነው፡፡ ስለዚህም እንላለን እኒህ ሰውዬ እንኳንም ተፈጠሩ፣ እንኳንም ኖሩ፣ እንኳንም መከሩ… ብዙ ዘመንም ይኑሩ! አሜን!
No comments:
Post a Comment