Pages

May 28, 2013

ወያኔ እና እኛ ሙስና ስንል

በቅርቡ በሀገር ውስጥ ገቢና በጉሙሩክ አገልግሎት መስሪያ ቤት የሚሰሩ ጥቂት ባለስልጣኖችና ተባባሪ የተባሉ ግለሰብ ነጋዴዎች፣ በሙስና ተወንጅለው ወህኒ መውረዳቸውን ተከትሎ ወያኔ ፀረ-ሙስና ድርጅት ለመምሰል ከተግባሩ የበለጠ የከበሮ ድምጽ እያሰማን ይገኛል። አንዳንድ የዋህም ይህን ከበሮ በመስማት ሙስናን ለማጥፋት ዘመቻ የተጀመረ መስሏቸው ተስፋ ሲያደርጉ ይታያል።
በመሰረቱ ሙስና በወያኔ ስርአት ውስጥ የስርአቱ መቆሚያ ምሰሶ ከሆነ ውሎ አድሯል። በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት እየተመናመኑ በሄዱበት ፍጥነት ነው ሙስና እየደራ የሄደው። ከላይ እስከታች በተዘረጋው የወያኔ ስርአት ውስጥ ከቁንጮ ባለስልጣናት እስከታችኛው አገልጋይ ድረስ በሙስና ያልተዘፈቀ የስርአቱ አገልጋይ መፈለግ ከዝንጀሮ ቆንጆ የመምረጥ ያህል ከባድ ሆኗል።
የወያኔ ትላልቅ ሙሰኞች ለምልክት ትንንሽ ሙሰኞችን አልፎ አልፎ በማሰር ፀረ ሙሰኛ መስለው ሊያሞኙን ቢሞክሩ ዛሬ የመጀመሪያቸው አይደለም። ወያኔ ሙስናን ክስ የሚጠቀምበት አንድም በውስጡ ካፈነገጡ ሃይሎች ጋር የፖለቲካ ልዩነትን ለማወራረጃ ወይም ለውጭ ለጋሾች ሙስናን የሚጠላ መስሎ ለመታየት ሲፈልግ ብቻ መሆኑን ከልምድ እና ከተግባሩ ህዝቡ ያውቀዋል።
የወያኔ መንግስት ሀገሪቱን ወደ ድህነት ማቅ ቁልቁል እያስገባና ሀገሪቱ በእዳ እያስያዘ፣ በአንጻሩ ግን የስርአቱ ቁንጮ ባለስልጣናት በሙስና ተዘፍቀው፣ በልፅገውና ከብረው፤ ራሳቸውን ከሙስና ነጻ ሆኖ ለመታየት ሲያሻቸው ግልገሎቹን በማሰር እና በራሳቸው ሚዲያ አስረሽ ምችው ይጨፍራሉ።
በእኛ እይታ ወያኔ ራሱ ቆሞ የሚሄድ ሙስና ነው። ወያኔና ሙስናን፣ ሙስናንና ወያኔን መለያየት አስቸጋሪም ነው። የወያኔ አባልና ደጋፊ የሚሰበሰበው፣ የሚመለመለው በመንግስት ሀብትና ንበረት ሰዎችን በማባበል ነው። ይህም ሙስና ነው።
ወያኔ ለየእለቱ የፖለቲካ ድርጅታዊ ስራውና በምርጫ ጊዜ በገፍ ካለ አቤት ባይ የሚጠቀመው የመንግስት ገንዝብ፣ ተሽከርካሪ፣ ነዳጅ፣ ቢሮ፣ የሚከፈለው የመንግስት ውሎ አበል፣ የሚገለገልበት የህዝብ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ጋዜጣ ወዘተ የሙሰኝነት ስርአታዊነቱ መገለጫ ነው። የመንግስት ስራ እድልን ከተማሩ ዜጎች ሳይቀር እየነጠቀ በዘርና በወያኔ አባልነት መለኪያ ለተመለመሉ አባሎች የሚሰጠው ስጦታ ዘግናኝ ሙስና ነው።
ኤፈርት የተባለው የወያኔ ኩባንያ ከህዝብና ከመንግስት በተዘረፈ ሀብት መመስረቱን እንደማያውቅ ትተን ትላንት ከባንክ ካለተከራካሪ እየተበደረ የሚነግድብን ንግድ፣ ሲከስር ብድሩና ወለዱን መክፈል ሲያቅተው ወያኔ ሙስና ብለን ይህን እንድንጠራው አይፈልግም።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ ተገዶ ወይም ተወግዶ በሀገራችን በህግና ህግ ብቻ የሚሰራ መንግስት መመስረትን እንደ ግብ የምንቆጥረው ለዚህ ነው። ግንቦት 7 በሀገራችን ሙስና ላይ የአመረረ ትግል ማድረግና ሙሰኞችን ማጥፋት የሚቻለው ወያኔን ያስወገድን እለት ብቻ ነው። ስለዚህም የሀገራችን ህዝብ ሆይ ይህን ተረድተህ ትግሉን በአስቸኳይ ትቀላቀል ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate