Pages

Jan 23, 2014

በሰብአዊ መብት አያያዝ አደጋ ላይ የወደቀው የኢትዮጵያ ገፅታ አሁን ደግሞ ተባብሷል ይለናል Human Right Watch በ2014



በሰብአዊ መብት አያያዝ አደጋ ላይ የወደቀው የኢትዮጵያ ገፅታ አሁን ደግሞ ተባብሷል ይለናል Human Right Watch በ2014 የዓለም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ፡-ኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በነሀሴ ወር 2012 ዓ.ም. መሞታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተተካው አዲሱ አመራር ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች እንደሚያደርግ ተጥሎ የነበረው ተስፋ ተዳፍኗል፤ በ2013 ዓ.ም ተጨባጭ የሆነ የፖሊሲ ለውጥ አልታየም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሃሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት እና በሰላም የመሰብሰብ ነጻነት ላይ የጣሉትን ጥብቅ ገደብ ማስፈጸማቸውን የቀጠሉበት ሲሆን የሲቪል ማህበራትን እና ነጻ መገናኛ ብዙሃንን እንቅስቃሴ ለማዳከም አፋኝ ሕጎችን ይጠቀማሉ፤ግለሰቦችንም ፖለቲካዊ መነሾ ያላቸውን ክሶች በመመስረት የጥቃት ዒላማ ያደርጋሉ።
መንግስት በሃይማኖታዊ ጉዳዮቻቸው ላይ ጣልቃ መግባቱን የተቃወሙ ሙስሊሞች ዓመቱን ሙሉ በጸጥታ ሃይሎች የዘፈቀደ እስር፣ እገታ፣ ድብደባ እና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ አያያዞች ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. የታሰሩት 29ኙ የተቃውሞው መሪዎች የፍርድ ሂደት ከጥር ወር 2013 ጀምሮ ለህዝብ፣ ለመገናኛ ብዙሃን፣ እና ለቤተሰብ አባላት ዝግ ተደርጓል፡፡ እጅግ አወዛጋቢና መሠረታዊ ግድፈት ያለባቸውን ድንጋጌዎች በያዘው የሃገሪቱ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ መሰረት ጥፋተኛ የተባሉ የተቃዋሚ መሪዎች እንዲሁም አራት ጋዜጠኞች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ከሃገር ውስጥ በሚገኝ ገቢ እና ከውጭ በሚመጣ እርዳታ በሚደገፉ ስፋት ያላቸው የልማት ፕሮግራሞች አፈጻጸም ምክንያት የአንዳንድ ማህበረሰብ ተወላጅ ነዋሪዎች ያለበቂ ምክክር ወይም ምንም አይነት ካሳ ሳይከፈላቸው ከመኖርያቸው እንዲፈናቀሉ ይደረጋል፡፡ የጸጥታ ሃይሎች ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው አንስተው ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ሃይል፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይፈጸማሉ፤ ለምሳሌ በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የሚገኙ ተወላጅ ነዋሪዎች ለዘመናት የኖሩበት መሬት መንግስት ለሚያካሂደው የስኳር መስኖ ልማት ይፈለጋል በሚል መፈናቀላቸው እንደቀጠለ ነው። በሰላም የመሰብሰብ ነጻነት ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር የሚይዙት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞ አድርገዋል፡፡ የተቃውሞው መነሻ ምክንያት መንግስት በእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ውስጥ እና በአዲስ አበባ በሚገኘው የአወሊያ መስጊድ ላይ ይፈጽማል የተባለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ነው፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎቹን ለመግታት መንግስት ሃይል ተጠቅሟል፤ የዘፈቀደ እስር እና ድብደባ በተቃዋሚዎቹ ላይ ፈጽሟል፤ እነዚህ ሕገ ወጥ ተግባራት በሀምሌ 2012 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው በጥቅምት 2012ዓ.ም በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት ክስ በተመሰረተባቸው 29 ታዋቂ የተቃውሞ እንቅስቃሴው መሪዎች ላይም ተፈጽመዋል፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደቱን መገናኛ ብዙሃንን፣ ዲፕሎማቶችን እና የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ህዝብ እንዳይከታተለው ከጥር ወር ጀምሮ ዝግ አድርጎታል፡፡ አንዳንዶቹ ተከሳሾች በእስር ላይ እያሉ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንደተፈጸመባቸው ተገልጿል። እንዲሁም እንዳንዶቹ ተከሳሾች ለሁለት ወራት ያህል የሕግ አማካሪ ወይም ጠበቃ ያላገኙበት ሁኔታና ከቤተዘመድ ጋር ለመገናኘት የነበረውን ችግር ጨምሮ የፍርድ ሂደቱ በሕግ በተቀመጡ ስርዓቶች አግባብ መካሄዱን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ በርካታ ግድፈቶች ተፈጽመዋል።
በተከሳሾቹ ላይ በመንግስት ቴሌቪዥን ውንጀላ እና ክስ ያለበት መረጃ በማስተላለፍ መንግስት ተከሳሾቹ ከፍርድ ውሳኔ በፊት ነጻ ሆነው የመገመት መብታቸውን የሚጋፋ ድርጊት ፈጽሟል። መንግስታዊ በሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ጃሃዳዊ ሃረካት የሚል ርዕስ ያለው ፕሮግራም በጥር ውስጥ የተላለፈ ሲሆን ፊልሙ ከተከሳሾቹ ውስጥ አምስቱ የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት በቁጥጥር ስር እያሉ የተቀረጸ ክፍል አካቷል። ፕሮግራሙ የተቃውሞው መሪዎችን እንደ አሸባሪዎች በመቁጠር የሙስሊሞቹን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከአክራሪ የእስልምና ሃይሎች ጋር አነጻጽሯል፡፡ እስሩ እንዳለ ቢሆንም በ2013ም ተቃውሞው ቀጥሏል፡፡ በነሃሴ ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የረመዳን ወር መጨረሻ የሆነው የኢድ አል ፈጥር በዓል በሚከበርበት ዕለት የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ የአይን እማኞች በአዲስ አበባ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ተሰማርተው እንደነበረ የገለጹ ሲሆን ታማኝ ምንጮች ደግሞ ሰልፈኞቹን ለመበተን ፖሊስ ከተገቢው በላይ ሃይል እንደተጠቀመ እና ለጊዜውም ቢሆንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን በቁጥጥር ስር አውሎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፎ አዲስ መጭ የሆነው ሰማያዊ ፓርቲ በሰኔ ወር ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል፤ ሰልፉ በስምንት ዓመት ጊዜ ውስጥ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የተዘጋጀ የመጀመሪያው ሰልፍ ነው፡፡ የጸጥታ ሃይሎች የሰማያዊ ፓርቲን ጽህፈት ቤት ጥሰው በመግባት በርካታ ሰዎችን በማሰራቸውና የፓርቲውን ንብረቶች በመውረሳቸው ምክንያት ፓርቲው በነሀሴ ወር ሊያካሂድ አቅዶ የነበረው ሰልፍ ተሰርዟል። ሰማያዊ ፓርቲ ቀደም ብሎ ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ ለመንግስት አቅርቦ የነበረው ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ነበር። የዘፈቀደ እስር እና ጎጂ አያያዝ የዘፈቀደ እስር እና በእስር ቤቶች የሚደረግ ጎጂ አያያዝ ከፍተኛ ችግር መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ተማሪዎች፣ የተቃዋሚ ጎራ አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ የሰላማዊ ሰልፍ ተሳታፊዎች እና ሌሎችም የመሰብሰብ፣ ሃሳብን የመግለጽ እና የመደራጀት መብታቸውን መግለጽ የሚፈልጉ ሰዎች በየጊዜው በዘፈቀደ ይታሰራሉ፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በፖለቲካ ምክንያት የሚያዙ ሰዎች ላይ በተለይም እነዚህ ሰዎች ከክስ ወይም ከፍርድ ሂደት በፊት በሚታሰሩበት እና ማዕከላዊ በመባል በሚታወቀው አዲስ አበባ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል ጎጂ አያያዝ ይፈጸማል፡፡ በሃይል በማስገደድ ከእስረኞች መረጃ፣ የእምነት ቃል እና ሃሳብ ለማውጣጣት እስከ ማሰቃየት የሚደርስ ጥቃት እና ሌሎች ጎጂ አያያዞች የሚፈጸሙባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። የተያዙ ሰዎች በተለይ ክስ ከመመስረቱ በፊት ብዙ ጊዜ የህግ አማካሪ እንዳያገኙ ይደረጋል፡፡ ያልተገባ አያያዝ የተፈጸመባቸው እስረኞች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከፍርድ ቤቶች የሚያገኙት መፍትሄ እጅጉን ውሱን ነው፤ አንዲሁም እስር ቤቶች እና ሌሎች የማቆያ ቦታዎች በገለልተኛ መርማሪዎች በመደበኛነት እንዲጎበኙ አይፈቀድም፡፡ ከመንግስት ጋር ቀረቤታ ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተወሰኑ እስረኞችን እና እስር ቤቶችን የጎበኘ ቢሆንም በማንኛውም ገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ወይም ሌላ ድርጅት መደበኛነት ያለው የክትትልና የምርምራ ስራ አይሰራም። በሃምሌ ወር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ የነበረው የአውሮፓ ፓርላማ የልዑካን ቡድን አባላት አስቀድሞ ፈቃድ ተሰጥቶአቸው የነበረ ቢሆንም አዲስ አበባ የሚገኘውን የቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዳይጎበኙ በባለስልጣናት ተከልክለዋል።
ሃሳብን የመግለጽ እና የመደራጀት ነጻነት በ2009 ዓ.ም የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ ከወጡ በኋላ በኢትዮጵያ ሃሳብን የመግለጽ እና የመደራጀት ነጻነት በከፍተኛ ደረጃ ተገድቧል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጁ በዓለም ላይ ካሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር ከወጡ በጣም አፋኝ ህጎች አንዱ ነው፡፡ በሰብዓዊ መብቶች፣ መልካም አስተዳደር፣ ግጭት አፈታት፣ እና የሴቶች፣ የህጻናት እና አካል ጉዳተኛ ሰዎች መብቶች ዙሪያ አድቮኬሲ የሚሰሩ ድርጅቶች ከጠቅላላ ገቢያቸው 10 በመቶ በላይ እርዳታ ከውጭ ምንጮች መቀበል እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ሕግ ሳቢያ እጅግ መልካም ስም የነበራቸው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ይሰሩ የነበረውን ስራ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሱ ሲሆን ሌሎቹም ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ስራዎችን መስራት ጭራሹኑ አቁመዋል። በርካታ ታዋቂ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች በተፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት ሃገሪቱን ለቀው ተሰደዋል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በከፍተኛ የመንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ፤ እንዲሁም በርካታ ጋዜጠኞች ራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ ያካሂዳሉ፡፡ መንግስትን በፅኑ የሚተቹ ድረ ገጾች እና ጦማሮች በመደበኛነት ይዘጋሉ እንዲሁም የውጭ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ስርጭቶች በተደጋጋሚ ይታፈናሉ። ለነጻ የሃገር ውስጥ ጋዜጦች የሚሰሩ ጋዜጠኞች የሚደርስባቸው ተከታታይ ጥቃት እና ማስፈራራያ እንደቀጠለ ነው።
የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ የፖለቲካ ተፎካካሪዎችን ለማጥቃት፣ ነጻ ሃሳብን ለማፈን፣ እንዲሁም ጋዜጠኞችን ዝም ለማሰኘት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በሐምሌ ወር 2012ዓ.ም የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በማሴር እና አሸባሪ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ በሚል በተከሰሰው ጋዜጠኛ እና ብሎገር እስክንድር ነጋ ፈንታ ላይ የተሰጠውን የ 18 ዓመት የእስር ቅጣት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በግንቦት ወር 2013 እንዲጸና ወስኗል። እስክንድር ‘የፔን’ የመጻፍ ነጻነት ሽልማትን በ2012 ተሸልሟል፡፡ የፍትህ ጋዜጣ ጋዜጠኛ የሆነችው ርዕዮት ዓለሙ ገቤቦ በጻፈችው ጽሁፍ ምክንያት በጸረ ሽብር ህጉ በተጠቀሱ ሶስት ክሶች ተከሳ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶባታል፡፡ በመጀመርያ ተፈርዶባት የነበረው 14 ዓመት በይግባኝ ወደ 5 ዓመት የተቀነሰላት ቢሆንም የቀረው የአምስት ዓመት ፍርድ ላይ ያቀረበችው ይግባኝ በጥር ወር ውድቅ ተደርጎባታል፡፡ ርዕዮት ከፍተኛ ዝና ያለውን የ2013 የዩኔስኮ ጉሌርሞ ካኖ የዓለም ፕሬስ ነጻነት ሽልማት ተሸልማለች፡፡ የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚያካሂዳቸውን የተቃውሞ ሰልፎችን ሲዘግቡ የነበሩ ጋዜጠኞች ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል እንዲሁም በዘፈቀደ ታስረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከህትመት ውጭ የሆነው የሙስሊሞች ጉዳይ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ሰለሞን ከበደ በጥር ወር የታሰረ ሲሆን የጸረ-ሽብር ህጉን አዋጅ በመጣስ ክስ ተመስርቶበታል፡፡ የጋዜጣው የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ዩሱፍ ጌታቸው በ2012 በተመሳሳይ ህግ ተከሷል፡፡ ሌሎች በርካታ ጋዜጠኞች በ2013 ከኢትዮጵያ ተሰደዋል፤ ይህም ሃገሪቱን በስደት ላይ ባሉ ጋዜጠኞች ብዛት ከዓለም ሶስተኛ ሃገር አድርጓታል፡፡
ከልማት ፕሮግራሞች ትግበራ ጋር በተያያዘ የሚፈጸም በሃይል ማፈናቀል የኢትዮጵያ መንግስት ከሚያካሂደው የሰፈራ መርሃ ግብር ጋር በተያያዘ አንደሚፈፀሙ የሚገለጸውን በደሎች መንግስትም ሆነ የለጋሽ ማህበረሰብ አባላት በበቂ ሁኔታ መመርመር አልቻሉም፡፡ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን አቅርቦት ለማሟላት በሚል ምክንያት በዚህ መርሃ-ግብር 1.5 ሚሊዮን የገጠር አካባቢ ነዋሪዎች ከመኖርያ አካባቢያቸው ተነስተው በሌሎች ቦታዎች እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡ ይሁንና መርሃ ግብሩ ተግባራዊ በተደረገበት በመጀመሪያው ዓመት በጋምቤላ ክልል አንዳንድ ቦታዎች የተካሄደው ሰፈራ በሃይል የተደረገ ሲሆን ድብደባ እና የዘፈቀደ እስር የተፈጸሙባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ከዚህም ሌላ የማስፈሩ ስራ የተካሄደው ከተነሺዎቹ ጋር በቂ ምክክር ሳይደረግ እና በቂ የካሳ ክፍያ ሳይፈጸም ነው። የዓለም ባንክን የአሰራር ተጠያቂነት የሚከታተለውና ከባንኩ ነፃ የሆነው የቁጥጥር ቡድን በስደት ላይ የሚገኙ የአኙዋክ ብሔረሰብ አባላት ባንኩ ጋምቤላ ውስጥ የራሱን የአሰራር ሁኔታዎች ጥሷል በማለት ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ በማለት ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ የዓለም ባንክ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ቦርድ በሐምሌ 2013 ተቀብሎታል። ይህ ሪፖርት በሚዘጋጅበት ወቅት ምርመራው በመካሄድ ላይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የሚኖሩ 200 ሺህ ተወላጅ ነዋሪዎችን ከመሬታቸው ላይ በማስለቀቅ በ245 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የስኳር ልማት ስራ ማከናወኗን ቀጥላለች። እነዚህ በጥምር ግብርና እና ከብት እርባታ የሚተዳደሩ ተወላጅ ነዋሪዎች ለዘመናት ከኖሩበት መሬት ተፈናቅለው በሰፈራ መርሃ ግብር አማካኝነት በቋሚ መንደሮች እንዲሰፍሩ ተደርጓል።
ዋና ዋና ዓለምአቀፍ አካላት ኢትዮጵያ ከውጭ ለጋሾች እና ከአብዛኞቹ የቀጠናው ጎረቤቶቿ ጋር መልካም ግንኙነት አላት፡፡ ይህ ጠንካራ ግንኙነት የተመሰረተው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ፣ ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በምታደርገው አስተዋጽኦ፣ ከምዕራብ ሃገራት ጋር በጸጥታ ጉዳይ ላይ ባላት ትብብር እና የተወሰኑ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን በማሳከት ረገድ ባስመዘገበችው እድገት ምክንያት ነው፡፡ ሃገሪቷ ያላት ይህ ጠንካራ ግንኙነት የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ በዝምታ እንዲያልፍ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በ2013ም ኢትዮጵያ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያላትን የአደራረዳሪነት ሚና የቀጠለች ሲሆን ወታደሮቿም በአወዛጋቢው አቢዬ ግዛት የሰፈነውን አስተማማኝ ያልሆነ ጸጥታ በማስጠበቅ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል። የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደሶማልያ ዘልቀው መግባታቸውን የቀጠሉ ቢሆንም ወታደሮቹ በዚያ የተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል አካል አይደሉም። ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ድጋፍ ከለጋሾች ማግኘቷን የቀጠለች ሲሆን በ2013 ያገኘችው ድጋፍ 4 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል፡፡ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች አንደመሆናቸው መጠን ለጋሽ ሃገራት እጅግ አስከፊ ሆነውን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አስመልክቶ ግን ዝምታን መርጠዋል። ከልማት መርሃ ግብሮች አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎችን አስመልከቶ የሚቀርቡ ክሶችን ለመመርመር የሚወስዱት እርምጃም እጅግ ውሱን ነው።
ግብጻዊያን ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ከናይል ወንዝ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ወደ ግድቡ ይቀየሳል የሚል ስጋት ስለገባቸው በ2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ እና የግብጽ ግንኙነት የበለጠ ሻክሯል። 85 በመቶ የሚገመተው የናይል ወንዝ ውሃ ምንጭ ኢትዮጵያ ስትሆን ግብጽ ደግሞ ለሚያስፈልጋት ማንኛውም የውሃ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በናይል ወንዝ ላይ ጥገኛ ነች፡፡ ግድቡ 6 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ይሆናል፡፡ የግድቡ ግንባታ የተጀመረው በ2012 ሲሆን በ2018 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከምዕራባዊያን ለጋሽ ሀገራት በተጨማሪ ቻይና፣ ህንድ እና ብራዚል የተለያዩ ከፍተኛ መጠን ላላቸው የልማት ስራዎች የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል። ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የውጭ የግል ኢንቨስትመንት እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን በ2013 የግብርና ንግድ፣ ሃይድሮኤሌክትሪክ፣ ማዕድን ማውጣት እና ነዳጅ ፍለጋ ኢንቨስትመንት ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ነው።የግብርና ንግድ ኢንቨስትመንት በዋናነት ከህንድ፣ ከመካካለኛው ምስራቅ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚመጡ ሲሆን የመሬት ዋጋው ዝቅተኛ መሆን እና ለጉልበት የሚከፈለው ዋጋ አነስተኛነት ባለሃብቶቹን የሚስብ ሆኗል። እንደ ሌሎቹ በርካታ ትልልቅ የኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ሁሉ እነዚህ መርሃ ግብሮች ሲተገበሩ ሰዎችን ከመሬታቸው በሃይል የማፈናቀል ተግባር ሊፈጸም ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ።

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate