የግንቦት ሰባት አራተኛ ጉባኤ አቋም መግለጫ
የግንቦት ሰባት የፍትህ ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አራተኛ ጉባኤ ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓም ተጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከተካሄደ በኋላ ህዝባዊ ትግሉን ወደፊት የሚያራምዱ ዉሳኔዎችን ካሳለፈ በኋለ ባለፈዉ ሰኞ ምሽት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ ተጠናቀቀ። ይህ የንቅናቄዉ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ንቅናቄዉ ባለፉት ሁለት አመታት የተጓዘባቸዉን መንገዶች፤ ያቀዳቸዉን ስራዎችና የዕቅዱን አፈጻጸም በጥልቀትና በስፋት በመዳሰስ መጪዉ የትግል ወቅት የሚጠይቀዉን የመስዋዕትነት ደረጃ ከወዲሁ ተመልክቶ ዘረኛዉን የወያኔ አገዘዝ በማስወገድ የኢትዮጵያን ህዝብ የፍትህና የዲሞክራሲ ጥማት ሊያረኩ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸዉን አበይት ዉሳኔዎች አሳልፏል።
የግንቦት ሰባት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ የንቅናቄዉን የአለፉት አምስት አመታት ጉዞና በዚህ በአራተኛዉ ጉበኤ ላይ የስልጣን ዘመናቸዉን የጨረሱት የንቅናቄዉ ምክር ቤትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የስራ ዕቅድና የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጦ ሰፊና ጥልቅ ዉይይት ካካሄደ በኋላ በጉባኤዉ ላይ አዲስ ለተመረጡ የአመራር አባላት ንቅናቄዉ የታሰበበትን ግብ እንዳይመታ አንቀዉ የያዙትን እንቅፋቶች እንዲያስወግድና እንዲሁም የንቅነቁዉ ጥንካሬ በታየባቸዉ መስኮች አቅሙን አጣናክሮ በይበልጥ በመስራት የኢትዮጵያ ህዝብ ከንቅናቄዉ የሚጠብቀዉን የታሪክ አደራ እንዲወጣ አሳስቧል። በጉባኤዉ ወቅት አባላት ያደረጉት አመራሩን የመንቀፍ፤አቅጣጫ የማሳየት፤ ሀሳብ የማመንጨትና በአጠቃላይ በእያንዳንዱ የጉባአዉ ስብሰባ ላይ ባሳዩት ንቁ ተሳትፎ ንቅናቄዉ በህዝባዊ አመጽና እምቢተኝነት ዘርፎች ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍም እያደገ መምጣቱን አሳይተዋል።
የግንቦት ሰባት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ የምክር ቤትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ እንዲሁም የስነ ስርአትና የግልግል ኮሚቴ ሪፖርቶችን አዳምጦ ሰፊና ጥልቅ ዉይይት ካካሄደ በኋላ ሪፖርቶቹን አጽድቋል። ከዚህ በተጨማሪ የንቅናቄዉን እስትራቴጂና ይህንኑ እስትራቴጂ ተሸክሞ በተግባር የሚተረጉመዉን መዋቅር በአጽንኦት ከፈተሸ በኋላ በስትራቴጂዉ ላይ መጠነኛ ለዉጥ በማድረግ የእስትራቴጂዉንና የመዋቅር ለዉጡን ተቀብሎ አጽድቋል። ይህ የንቅናቁዉ አራተኛ ጉባዜ ንቅናቄዉን ላለፉት ሁለት አመታት የመሩትንና ያገለገሉትን የምክር ቤት፤ የኦዲትና ቁጥጥር፤ የስነ ስርአትና ግልግልና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግኖ በማሰናበት በምትካቸዉ ንቅናቄዉን ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት የሚያገለግሉ የምክር ቤት አባላት፤ የኦዲትና ቁጥጥር፤ እንዲሁም የስነ ስርአትና ግልግል ኮሚቴ አባላትን መርጧል።
አራተኛዉ የግንቦት ሰባት መደበኛ ጉባኤ ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበትን ሁኔታ በዝርዝር ከቃኘ በኋላ ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ዉጊያ የተያያዘዉ አገር ዉስጥና በዉጭ አገሮችም ስለሆነ ወያኔን በእነዚህ ሁለት የትግል መስኮች እንደአመጣጡ ከገጠምነዉ የሚሸነፍ ድርጅት መሆኑን ሙሉ በሙሉ በመቀበል አባላቱ ባሉበት ቦታ ሁሉ የሚሰሩት ስራ ወያኔን በማስወገድ ላይ እንዲያተኩር አሳስቧል። ከአለም ዙሪያ ከተለያዩ አገሮች የመጡ የግንቦት ሰባት አባላትን ያሰባሰበዉ አራተኛዉ የግንቦት ሰባት መደበኛ ጉባኤ የትግል ቃል ኪዳን የታደሰበት፤የመስዋዕትነት ዝግጅት የታየበትና አባላት የትግልና የስራ ልምድ የተላዋወጡበት ከምን ግዜዉም ባላይ የተሳካና የተዋጣለት ጉባኤ ነበር። በመጨረሻ ጉባኤዉ የግንቦት ሰባት የፍትህ ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አራተኛ ጉባኤ ለአባላቱና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ የትግል ጥሪ በማስተላለፍ ደማቅ በሆነ ስነሰርአት ተፍጽሟል።
የግንቦት ሰባት የፍትህ ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ