ከዘር ማንነታችን በፊት ሰብአዊ ሰውነታችን፤ ከጎጠኝነታችን በፊት ኢትዮጵያዊነታችን፤ ከሸፍጥ፤ ከተንኮል፤ ከመሰሪነታንችን በፊት ቅንነታችን፤ ከፍርሀታችን በፊት ድፍረታችን፤ እርስ
በርስ ከመጠራጠራችን በፊት መተማመናችን፤ ከመፍረክረካችን በፊት በጽናት መቆማችን፤ ከልዩነታችን በፊት አንድነታችን፤ ወያኔ ዛሬ ኢትዮጵያውያንን ከከተተበት መቀመቅ ውስጥ የሚያወጣን ብቸኛ መፍትሄ ከላይ የደረደርኩት ነገር ብቻ የመስለኛል።
ነጻ አውጭ ነን የሚሉ የዘር ፖለቲከኞች፤ ህዝብ መክሮ ዘክሮ ከዚህ ዘር ነጥሉን፤ ከዚያ ዘር ነጥሉን፤ ነጻ አውጡን፤ ብሎ ባይመርጣቸውም፤ በስራቸው ለማሰባሰብ ለፈለጉት ህዝብ ታሪክ እየፈጠሩ መስበካቸው እንዳለ ሆኖ፤ እንዲዋጋላቸው፤ እንዲታገልላቸው ሲያደርጉም የዚያኑ ያህል የውሸት ተስፋ እየመገቡም ነው። ለምሳሌ በትግሉ ዘመን የሻእቢያ ካድሬዎችና ፕሮፓጋንዳ ሰራተኞች ዘወትር ህዝቡን ሲሰብኩ፤ ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ እያንዳንዱ ኤርትራዊ ዜጋ ምንም ስራ ሳይሰራ ከወደቦች በሚገኝ ገቢ ብቻ በቀን ከሰላሳ እስከ አርባ ብር ገቢ ይኖረዋል እያሉ ይሰብኩ ነበር። ከነጻነት በኋላ ኤርትራ የምስራቅ አፍሪካ ሲንጋፑር ትሆናለች ይሉ ነበር። እነሆ ነጻነቱ ሀያ ሁለት አመታትን አስቆጠረ፤ የኤርትራ ህዝብ በቀን ሰላሳ ብር በነፍስ ወከፍ እየታደለው ነው? ኦሮሞን ነጻ እናወጣለን የሚሉትን ሰዎች ብትሰሟቸው ወርቁ፤ ቡናው፤ ማእድኑ የብቻቸው እንደሚሆንና ከነጻነት በኋላ እንደሚበለጽጉ ነው የሚቀባዥሩት። ኦጋዴንን ነጻ እናወጣለን የሚሉትን ሶማሌዎች ብትሰሟቸው ጋዙ፤ ነዳጁ የብቻችን ይሆናል ከነጻነት በኋላ እያንዳንዱ ሰው ይበለጽጋል ነው የሚሉት። የብቻ ተጠቃሚነት ቅዥት፤ ስግብግብነት፤ ራስ ወዳድነት፤ በነጻነት ስም የቡድን ጥቅም የስልጣን ምኞት ቅዥት።
አንድ ህዝብ አንድ ቋንቋ ስለተናገረ፤ አንድ ባህል ስለተጋራ፤ ባንድ አካባቢ ስለኖረ፤ ምንጊዜም አብሮ በሰላም ይኖራል ማለት አይደለም። ርእዮተ አለም፤ ሀይማኖት፤ ጥቅም፤ ስልጣን፤ ንኡስ ነገድ፤ የአካባቢ ልዩነት፤ በሰው ልጆች መካከል ግጭትና አለመግባባትን፤ ብሎም ጦርነትና ፍጅትን ለመፍጠርም ሆነ ለማስነሳት በቂ ሀይል አላቸው። ሶማሌዎች አንድ ቋንቋ፤ አንድ ባህል፤ አንድ መልካምድር የሚጋሩ ናቸው።ለምንድነው አብረው መኖር ተስኖአቸው መንግስት አልባ ሆነው የቀሩት?
ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም “አቡሸማኔው ትውልድ” በሚለው የእንግሊዝኛ ጽሁፋቸው ውስጥ እንዳስቀመጡት “…ከኢትዮጵያ ህዝብ አርባ አንድ ሚሊዮን የሚሆነው እድሜው ከአስራ ስምንት አመት በታች እንደሚሆን ይገመታል። ካጠቃላዩ ህዝብ ከግማሽ በላይ ማለት ነው። ዩኒሴፍ የተባለው የህጻናት መርጃ ድርጅት እንደሚገምተው ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናቶቻችንን ከግማሽ በላይ የሚገላቸው የምግብ እጦት ነው። ኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ ወላጅ አልባ ህጻናት አሏት። 800 000 ያክሉ ወላጆቻቸውን ያጡት በኤድስ በሽታ ምክንያት እንደሚሆን ይገመታል። በከተሞች አካባቢ የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር 70 በመቶ በላይ መድረሱ ይገመታል። በ2011 የወጣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው 77.8 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮን የሚገፋው በቀን ከሁለት የአሜሪካን ዶላር ባነሰ የገንዘብ አቅም ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ስራ ለማግኘት፤ ለመኖር ሲሉ፤ ራሳቸውን ለመሸጥ ይገደዳሉ። በ 2010 የወጣ የአሜሪካ መንግስት የሰባዊ መብት ሪፖርት እንዳመለከተው የኢህአደግ ድርጅት አባል ያልሆነ ወጣት ስራ ለማግኘት ከቀበሌ የድጋፍ ደብዳቤ አያገኝም። ትምህርት ለመማር፤ ስራ ለመቀጠር፤ በግል ስራ ለመሰማራት የፓርቲ አባልነት መስፈርት ሆኖ ተቀምጧል።…..”
ታዲያ ለዚህ ትውልድ እየመሸ ነው እየነጋ? ለዚህች አገር እየመሸ ነው እየነጋ ? የጥቂት ህውሀት መሪዎችና ቅጥረኞቻቸው ህይወትና እድል እየለመለመና እያማረ ሲሄድ፤ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት እየጨለመና እያሽቆለቆለ ሲሄድ፤ የመላው ኢትዮጵያ ወጣቶች የነገ ህይወት ጸሊም ተስፋ ተጋርዶበት፤ አስፈሪውን መጪ ጊዜ ሁላችንም እያየነው ተነስተን አንድ ነገር ማድረግ የተሳነን ለምን ይሆን?
በሚሊዮኖች ለሚቆጠረው ወጣት ትውልድ በዚህ ዘረኛ ገዢ ቡድን ምክንያት ህይወት ጭለማ ከሆነችበት፤ የተፈጥሮ መብቱን፤ የዜግነት መብቱን በጥቂት ማፊያ ቡድን ካስነጠቀ፤ የወደፊት ህይወቱን፤ እድሉን፤ የጋራ ሀገሩን ለዚህ አጥፍቶ ጠፊ የዘረኞች ቡድን መቆመሪያ አሳልፎ ከሰጠ፤ ይህ ወጣት እንዴት ለሀገሩና ለወገኑ መድህን ሊሆን ይችላል? ወጣትነት ለውጥ ፈላጊነት ነው። ወጣትነት አዲስ ነገር ናፋቂነት ነው። ወጣትነት የሀገር ተረካቢ ባላደራነት ነው።
በ1998 እኤአ ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመንግስታቸው ጋር ከፍተኛ ግጭት የፈጠሩበትና ከፖሊስ ጋር አደባባይ የተፋለሙበትን አንድ አጋጣሚ ላንሳ፤ በዚያን ጊዜ የነበረው የሞይ መንግስት የሆነ መሬት ለኢንቨስተሮች በሊዝ ሊሸጥ ይስማማል። ወዲያው ጉዳዩ ለህዝብ ውይይት ይፋ እንደተደረገ፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከየተቋሙ በቁጣ ተፈንቅለው ድርጊቱን ለመቃወም ያልተፈቀደ ሰልፍ ይወጣሉ። የተማሪዎቹ ቁጣ ሊሸጥ የታሰበው መሬት በደን የተሸፈነና ለአራዊትም መኖሪያ ለተፈጥሮውም ጥበቃ ሀገሪቱን የሚጠቅማት በመሆኑ፤ “ሀገራችንን ነገ የምንረከብ እኛ ስለሆን፤ ይህ መንግስት ሀላፊነት የጎደለው ስራ እንዲሰራ አንፈቅድም፤ ለም መሬታችን ለማይረባ የባእድ ኢንቨስትመንት አይሸጥም” በማለት አደባባይ ወተው ከመንግስታቸው ጋር ግብግብ ገጠሙ። ህዝቡም ከያቅጣው ደገፋቸው። መንግስት አቋሙን ቀይሮ ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ተገደደ።
ድፍን ኢትዮጵያ እለት በእለት ሲቸበቸብ የኛ ተማሪዎች በዘር ተቧድነው በድንጋይ ይደባደባሉ። ወያኔ መላውን የሀገራችንን ምድር ከየትም አለም እየጠራ፤ ስለአጭር ጊዜም ሆነ ስለረጅም ጊዜ ጉዳቱ ምንም አይነት ጥናትና የህዝብ ውይይት ሳያደርግ በርካሽ ምድራችንን መሸጡን ቀጥሏል። ከሰላሳ አምስት በላይ ከሚሆኑ አገሮች ለሚመጡ ወይም ለመጡ 8000 በላይ ባለሀብቶች የንግድ እርሻ ፍቃድ አድሏል። መሬቱ ለባለሀብቶቹ ሲሰጣቸው፤ ዜጎች ከቀያቸው በሀይል እንዲወጡ፤ መኖሪያቸው እየፈረሰና ልጆቻቸው ደጅ እየተበተኑ፤ እንዲፈናቀሉ እየተደረገ፤ እንቢ ካሉ እየታሰሩ፤ እየተገረፉና እየተገደሉ ነው። በቅርቡ 150 የሚሆኑ የሰሬ ብሄረሰብ ወገኖቻችን በወያኔ ሚሊሺያ ተጨፍጭፈው መሬቱ ለባእዳን ባለሀብቶች ጸድቶላቸዋል። በሚቀጥሉት አስርና አስራአምስት አመታት ውስጥ ወያኔ ስልጣን ላይ ከቆየ ለራሳችን ፍጥነቱን የማንቆጣጠረው የህዝብ ብዛታችን ሲፈነዳ፤ መሬታችን ሁሉ በባእዳን እጅ ገብቶ የምናርሳት ኩርማን መሬት ቀርቶ፤ መቆሚያ መቀምጫ እንደምናጣ ለመተንበይ ነብይ መሆን አያስፈልግም። ለመኖር ስንል ሀገራችንን ከወረራት አለም ጋር ጦርነት መግጠማችን የማይቀር ነገር ነው። ወያኔ በመርዝ እንዲያልቁ ካላደረጋቸው የህዝባችን ብቻ ሳይሆን የቤት እንስሳቶቻችንም ቁጥር ያድጋል፤ ወደፊት የሚሰማሩበትም ቦታ ይጠፋል። ዛሬ ወያኔ ብቻ ነው ዋናው ገዳያችን። ያኔ ግን እርሻቸውንና ሀብታቸውን ንብረታቸውን የሚጠብቁት የአለም ሀብታሞች ወታደሮቻቸውን ልከው ያግዙታል። በደንብ እንገደላለን።
ያሁሉ ከመምጣቱ በፊት፤ ኢትዮጵያዊው ወጣት ትውልድ ዛሬ ላይ ቆሞ እየተጓዘበት እየቀረበው የመጣውን ጨለማ ጊዜ መመልከት ከቻለ፤ ፈጥኖ መነሳትና ህብረተሰቡን አስከትሎ የወያኔን መንግስት ማስወገድና ሀገሪቱን ማዳን መጪውን የጨለመ ተስፋ ወደ ብርሀን መለወጥ አለበት። በዘር ተከፋፍሎ መናቆሩን ከቀጠለ፤ እርስ በርሱ ሲባላ ወያኔና የባእድ ሽርካዎቹ ቅርጥፍ አድርገው በልተውት ምድሪቷን ያለስጋት ይኖሩባታል።
አቶ አስገደ ገብረስላሴ “መለስ ከደደቢት እስከ ህልፈት” በሚለው የጽሁፍ ስራቸው ውስጥ እንዳስቀመጡት፤ “….የሀገራችን መሪዎች ልጆችና ዘርማንዘራቸው በመንግስት ባጀት ያለ አንዳች የትምህርት ውድድር በቻይና፤ በአሜሪካ፤ በአውሮፓ፤ በደቡብ ኮርያ፤ ከፍተኛ ትምህርት በሚማሩበት፤ ፍትሀዊ የሆነ የሀገር ሀብት ክፍፍል በሌለበት፤ የሀገራችን ሀብት በህውሀትና ግብረአብሮቻቸው በባለቤትነት በተያዘበት፤ ህዝብ መጠለያ የማግኘት መብት ባጣበት፡ህብረተሰብ በሙሉ በግድ የህውሀት ኢህአደግ አባል ካልሆነ የማይኖርበት ሀገር ሆና እያለች፤ የትምህርት ነጻነት በሌለበት፤ የትምህርት ተቋማት ሁሉ የህውሀት ኢህአደግ አባላት መመልመያና ማደራጃ በሆነበት፤ የሴፍቲ ኔት፤ የድርቅ፤ ማናቸውም እርዳታ ሁሉ ለህውሀት አባላትና ደጋፊዎች ብቻ የሚሰጥበት፤…ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሁለተኛ ዜጋ የሆኑበት ሁኔታ እያለ መለስ እንዴት ዲሞክራሲያዊና ተራማጅ ሊባል ይችላል?….”
ዛሬ ስልጣን ላይ ተጣብቀው ሞት ነው የሚያስለቅቀን የሚሉት የትግራይ ናዚዎች ስልጣኑን ላለመልቀቅ ሲሉ የኢትዮጵያን ህዝብ እየገፉ የሚወስዱበት መቀመቅ አሁን ካለንበት ከደረስንበት ቦታ ላይ ቆመን የነገውን ስንመለከተው ወለል ብሎ የሚታይና የተለያዩ መድረሻዎችም ያለው ነው።
አንድ ሁለት እውነታ ላንሳ። ሩዋንዳ ውስጥ ሶስት ዘሮች አሉ። ሁቱ፤ ቱትሲና ቱዋይ ። እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1919 አም ጀርምኖችን ተክተው የበልጅየም ቅኝ ገዢዎች ሩዋንዳን ተቆጣጠሩ። ከሌሎች የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጋር ሲነጻጸሩ ቤልጅየሞች እጅግ ጨካኝና ግፈኛ ቅኝ ገዢዎች መሆናቸው ይነገራል። ስለተቆጣጠሩት አገር ህዝብ ምንም አይነት ደግነት የላቸውም። ላገሩ የተፈጥሮ ሀብት፤ ለህዝቡ ባህል፤ ለመሬቱ … ወዘተ። ዋናው እስትራቴጂያቸው ከህዝቡም ከመሬቱም ማናቸውንም ጠቃሚ ነው ብለው ያመኑትን አገራቸው ቤልጅየምን የሚገነቡበትን ሀብት መቦጥቦጥና ወደሀገራቸው ማሻገር ብቻ ነበር። ልክ ያለፈ ሀያ ሁለት አመታት ጀምሮ ወያኔ እያደረገ እንዳለው ሁሉንም ነገር ለትግራይና ወደትግራይ ክልል ማለት ነው። ቤልጂየሞች እንደመጡ ጀምሮ የነዋሪዎቹን የዘር ግንድ ልዩነት ሲያጠኑ ቆይተው በ1933 ላይ ሁቱ የትኛው ቱትሲ፤ ትዋይ አውቀው ሲጨርሱ፤ ሁሉም በየብሄረሰቡ መታወቂያ እንዲሰራለት፤ ሩዋንዳዊ ነኝ ሳይሆን የተለጠፈለትን የዘር አይነት እንዲጠራ ተደረገ። አሁን የኛ ቅኝ ገዥዎች ጀግኖቹ የትግራይ ፍልፈሎች እንዳደርጉን ማለት ነው። ሁቱዎች ብዙሀን ናቸው። ቱትሲዎች ሀዳጣን ናቸው 15%። የኛ ትግሬዎች እንዲያውም ከዚያ ያነሱ ናቸው 5%። አምስት እጅ የምለው አጠቃላዩን የትግራይ ህዝብ እንጂ በጦር ሀይል አገሪቱን ተቆጣጥረው በመግዛት ላይ ያሉትን ጥቂቱን የህውሀት መሪዎች አይደለም። በማናቸውም ጽሁፌ ውስጥ እማወራው የትግራይን አርሶ አደርና ሰራተኛ ህዝብ አይመለከትም። ህዝቡ ለራሱ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ በከፋ መልኩ ታፍኖ ተረግጦ የሚኖር ነው። ቤልጂየሞች የከፋፍሎ መግዛቱን ሂደት ሲያስተካክሉ ቱትሲዎችን ቀድሞውንም የሀገር ባላባት ሆነው ራሳቸውን ከፍ አድርገው ይኖሩ የነበሩትን አቀፉና ብዙሀኑን ሁቱዎችን ገሸሽ አደረጉጓቸው። የወያኔ ገዢዎቻችን ትግሬን አቀፉ፤ የቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ አርባ ክንድ አራቁት። የመንደር፤ የጎሳ፤ የአካባቢ መሪ ተብለው ህዝቡ የሚያውቃቸውን የሚቀበላቸውን በሙሉ ቤልጂየሞች እያባረሩ በምትካቸው በታማኝነት የሚመለምሏቸውን ሀዳጣን ቱትሲዎችን አስቀመጡ። ወያኔ በሀገራችን እያደረገ እንዳለው ማለት ነው።
የትምህርት እድሉን፤ የመንግስቱን ስራ ሀላፊነትና ተቆጣጣሪነት፤ በማናቸውም መስክ በጥቅማጥቅሙም “በዝምበለው ይውሰድ” ንቅዘቱም የበላይነቱን ለቱትሲዎቹ ሰጧቸው። የወያኔ ገዢ ቡድን ከትግራይ የሚመለምላቸውን ሁሉ በማናቸውም የኢትዮጵያ ክፍል የበላይ እንዳደረገው፤ ቤልጅየሞችም ቱትሲዎችን አጠናከሩ። ቤልጂየሞች ከሌላው ወገን ለሆዱ የተገዛውንና ከተጠቀመ ለጥፋት ስራቸው ሁሉ ፍጹም ተባባሪ ለመሆን የቆረጠውን ትንሽ ትንሽ እያላሱ፤ የገዛ ወገኑን መቀጥቀጥ የሚችል መዶሻና ድንጋይ አደረጉት። አሁን በየክልሉ ወያኔ በአምሳሉ የፈጠራቸው የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የሀረሪ፤ የሶማሌ፤….ወዘተ አይነት ደደቦችና ጅቦች።
ታዲያ ብዙሀኑን የሩዋንዳ ህዝብ ሁቱዎችንና ቱዋዮችን ያስከፋቸውና ለበቀል ያነሳሳቸው ነገር፤ ህዳጣኑ ቱትሲዎች የቅኝ ገዚዎችን ከለላና ድጋፍ በማግኘታቸው ብቻ ከሌሎች ወገኖቻቸው ተለይተው ተጠቃሚ በመሆናቸው ብቻ፤ ከቅኝ ገዢዎቹ ብሰው ወገኖቻቸውን የሚረግጡ፤ የሚገፉ፤ የሚጨቁኑ ሆኑ። አሁን በሀገራችን ህውሀት ስር ተለጥፈው የሚጥሉላቸው ቅንጥብጣቢ ብሶባቸው፤ ሆዳቸው ስለሞላ ብቻ ህሊናቸው ታውሮ፤ በወያኔ ትእዛዝ የገዛ ወገናቸውን የሚገሉ፤ የሚያፈናቅሉ ኢትዮጵያውያንን አይነት ማለት ነው።
በ1950 ዎቹ ቱትሰዎችንና ቅኝ ገዢዎቹን የሚያጣላ ሁነት ተከሰተ። በመላው አፍሪካ የተነሳው የነጻነት እንቅስቃሴና፤ አንዳንድ ተደማጭ የሀይማኖት አባቶች ስለነጻነት ህዝቡን ማነሳሳታቸው፤ ቱትሲዎች በቤልጂየሞች ላይ የእንቢታና የመነሳሳት፤ የነጻነት ጥያቄም አነሱ። በዚህን ጊዜ ለሩዋንዳ ነጻነት የሚንቀሳቀስ የሁቱዎች ፓርቲ ነበር። ቤልጂየሞች ገልበጥ አሉና እሳትን በሳት እንዲሉ ቀድሞ በእንክብካቤ ይዘው ከፍከፍ ያደረጓቸውን ቱትሲዎች ማግለልና የሁቱዎቹን ንቅናቄ መደገፍ ጀመሩ።
በሁቱና ቱትሲ ወንድማማቾች መካከል ይህ መጨካከን ይህ መገፋት፤ በተለያየ ጊዚ ብዙ ደም ያፋሰሰ ግጭት አስነስቶ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ የሀገሪቱ ተወላጆች እልቂት መክንያት ሆነ። 1961 ከነጻነት በሁዋላ ሁቱዎች እንደገና በቤልጂየሞች ድጋፍ ስልጣኑን ተቆጣጠሩ። የበቀል አዙሪቱ ቀጠለ። በጋራ ሀገራቸው ስልጣኑን ተጋርተው በሰላም ሀገራቸውን ማስተዳደሩ ተስኗቸው በስልጣንና በጥቅም ህሊናቸው ታውሮ እንደሰው ማሰብ ተስኗቸው እንደ አውሬ ሁነው እንደገና ሁቱዎች ደሞ በተራቸው ቱትሲዎችን ያሳድዱ ይጨቁኑ ጀመር። ቱትሲዎች ሽሽት ወደየጎረቤት አገራት መበተን ጀመሩ። ከ1961 እስከ 1964 ብቻ ቱትሲዎች አስር ጊዜ ከጎረቤት አገር እየተንደረደሩ ሁቱዎችን ለማጠጥቃትና ወደ ስልጣን ለመመለስ ሞክረዋል። ይህ ሙከራ ደግሞ በሀገር ውስጥ የቀሩ ቱትሲዎች በበቀል እንዲጨፈጨፉ ምክንያት ሆነ። እንዲህ እንዲህ እያለ ቅኝ ገዢዎች ስራ ላይ ያዋሉት እየከፋፍሉ እያጋጩ መግዛት የህብረተሰቡ ቋሚ በሽታ ሆኖ አረፈው።
እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1994 በሁቱዎች የበላይነት የሚመራው የሩዋንዳ መንግስት በቱትሲ አማጽያን መሪው ሲገደል፤ በቱትሲዎች ላይ ያንቀሳቀሰው የዘር ማጽዳት ዘመቻ ቀድሞውንም የታለመ የታቀደ ነበር። ለረጅም ጊዜ በሀገሪቱ ሬዲዮና ጋዜጦች ሁቱዎችን ኢላማ ያደረገ የዘር ጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በይፋ ይነዛ ነበር። “ሁቱዎች ከዚች ምድር ተጠራርገው ካልጠፉ ሩዋንዳ ሰላም አይኖራትም” ይሉ ነበር። ህውሀት በአማራው ህዝብ ላይ አሁንም በተለይ በትግራይ ክልል የማያቋርጥ የሬዲዮና የህትመት ፕሮፓጋንዳ፤ የዘር ጥላቻ ትምህርት ይሰጣል። እርግጥ ኢትዮጵያ በሽፍቶች የተያዘች ሀገር በመሆኗ ህግ የለምና ነው እንጂ ይህ የህውሀት ቀንደኛ መሪዎች በህዝቡ ውስጥ የሚረጩት መርዝ እድሜልክ ወህኒ መቀመቅ እንዲያርፉ የሚያደርጋቸው ነበር። ደጉ ነገር የኢትዮጵያ ህዝብ ከነሱ የቀደመ በመሆኑ የሚፈልጉትን የሚያስቡትን ነገር አያደርግላቸውም።
ወያኔ በህብረተሰቡ ውስጥ እያበረታታና እያስፋፋ ያለው እስከዛሬም ያከናወነው ዘርን ከዘር ሀይማኖትን ከሀይማኖት የማጋጨት ስራና እስትራቴጂ ባይዝለትም ተስፋ ይቆርጣል ማለት አይደለም። ተስፋውንና እስትንፋሱን የሚቆርጠው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ተነስቶ ጉሮሮውን ያነቀ እለት ብቻ ነው። በሰላማዊ አመጽም በሉት እሱ በሚያውቀውና በሚገባው አይነት። ለዚህም ተግባር ፊት አውራሪ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ ወጣት ዛሬ ነገ ሳይል ሁሉም ወደተመቸው የትግል ስልት ተካቶ ህብረተሰቡን በመምራት ለውጥ ማምጣት ግድ ይለዋል።
የደቡብ አፍሪካውን አፓርታይድ ታሪክ ላንሳ። በአስራሰባተኛው ክፍለ ዘመን በደቾችና በእንግሊዞች የቅኝ አገዛዝ ስር በነበሩበት ወቅት፤ በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው ከፋፍሎ የመግዛት ስልት፤ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ1948 ጀምሮ አፓርታይድ የመንግስቱ ይፋ ፖሊሲ ሆኖ በህግ ተደነገገ። ህዝቡ አንገዛም በማለቱ ህዳጣኑ ነጮች (ከእንግሊዞችና ደቾች ተዳቅለው እዚያው የተራቡ)፤ የደቡብ አፍሪካ ህዝብ በዘሩ እየተለየ የሚሰባሰብበት ክልል አዘጋጁ። የሀገሪቱን ዜጎች በአራት መደቧቸው። ነጮች፤ ጥቁሮች፤ ክልሶች፤ አና እስያውያን። ባንቱስታን በሚል የሚታወቁ አስር ትንንሽ አካባቢዎችን ከፋፍለው 75% ለሚሆነው ጥቁር ህዝብ፤ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ስፋት 13% በሚሆን ክልል ውስጥ አጎሩት። ሀይል በተቀላቀለበት ሁኔታ ወደየ ክልላቸው እንዲሰባሰቡ ተደረገ። አሁን ወያኔ በአማራው ህዝብ ላይ እያንቀሳቀሰ ያለው ንብረት እያስቀማ ወደ ክልላቸው እንዲባረሩ የማሳደድ እርምጃ፤ አፓርታይድ ያደርገው የነበረ፤ ሁሉንም ወደከለለት አካባቢ የማካተት ስራ አይነት ነው። ከህዳጣኑ ነጮች በስተቀር ማናቸው ወገን የፖለቲካ ውክልናም ሆነ ተሳትፎ በኢኮኖሚ በህግ እኩልነት እንደማይኖረው ደነገጉ። ባንቱስታንስ በሚል ለጥቁሮቹ የተከፋፈሉ የጎሳ አካባቢዎችን ከከለሉላቸው በኋላ የደቡብ አፍሪካ ዜጋ መሆናቸው ተሰርዞ፤ የየንኡስ ነገዳቸው አባልና ክልል ዜጋ የመሆን መብት ብቻ ሰጧቸው። ነጮቹ ይህንንም ያደረጉት ጥቁሮች፤ ራሳቸውን የደቡብ አፍሪካ፤ የገዛ አገራቸው ዜጋ አድርገው መቁጠር እንዲያቆሙ፤ ብሎም የፖለቲካ ተሳትፎና እኩልነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ነበር። የህዳጣኑን ነጮች የበላይነት የበለጠ ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ነበር።
ወያኔ ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ “ዜግነት” የሚለውን ቃል “ብሄረሰብ” በሚለው የጥፋት ቋንቋው የለወጠበት ዋና ምክንያት፤ የኢትዮጵያዊነት እምነትና አስትሳሰብ በሂደት ከህዝቡ ውስጥ ይጠፋል በሚል ከንቱ ምኞት ነው። የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ እንዳደረገው፤ ኢትዮጵያውያንም ኢትዮጵያዊነታቸው ተሰርዞ ማንነታቸው በየጎጣቸው ተወስኖ ይቀራል የሚል መለስ ስብሀት የፈጠሩት ከንቱ ራእይ አለ። ይሁንና እነሱ ይጠፋሉ እንጂ የኢትዮጵያዊነት ኩራትና ክብር ከእውነተኛ ኢትዮጵያውያን ደምና ስጋ ውስጥ አይጠፋም። የሚኒሊክን ሀውልትም ቢያፈርሱት፤ የአቡነጴጥሮስንም ሀውልት ቢያፈርሱት፤ የአሉላ አባነጋንም ሀውልት፤ ቢንዱት፤ ስድስት ኪሎ የቆመውን የሰማእታት ሀውልት አፍርሰው ጣሊያንንም ቢያስደስቱት፤ ለሺዎች ዘመናት በኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ የተገነባችውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከቶም ከቶ ከዜጎች ልብ ውስጥ ሊያፈርሱት አውጥተው ሊጥሉት አይችሉም። ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንደተባለው ዛሬ ክፉ ቀን ለወያኔ መሪዎች አድልቷልና እስከምናጠፋቸው ታሪካችንን መለያ ቅርሶቻችንን ማጥፋታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። በህውሀት ማቃብር ላይ መልሰን ብንገነባቸውም።
የደቡብ አፍሪካ ህዳጣን ነጭ ገዢዎች ያኔ ነጮችና ጥቁር ልጆች አብረው ትምህርት ገበታ ላይ እንዳይቀመጡ አደረጉ። አገልግሎት መስጫ ተቋማት፤ ህክምናና የመዝናኛ ስፍራዎች ሳይቀር ዝቅ ባለ ደረጃ ለብቻቸው ሰሩላቸው። የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች የነሱ ወዳልሆ ክልል ለመጓዝ የይለፍ ወረቀትና የዘር መለያ መታወቂያ የግድ አስፈላጊ ሆነ…. ለጥቁሮቹ ብቻ።ያ ከሌለ ከክልሉ ወደሌሎች ክልል ለመዝለቅ የሞከረ ጥቁር እስርና ቅጣት የሚጠብቀው ሆነ።
አሁን ኢትዮጵያውያን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል። በተለይ አማራና ኦሮሞ የሚተኮርባቸው ሲሆን፤ የሌላ ክልል ዜጎችም ቢሆኑ ወደ አፋር ክልል ወደ ሶማሌ ክልል ወደ ትግራይ ክልል ሄዶ እንደልቡ በነጻ መንቀሳቀስ አይችልም። የአካባቢው ፖሊሶች በስነስራት እንግዳ የሆነባቸውን ሰው አስቁመው ዘሩን፤ አድራሻውን፤ ከየት እንደመጣ ለምን እንደመጣ ይጠይቃሉ። የሚነጠቅ ነገር እንዳለው ካረጋገጡም ያለምንም ምክንያት አስረው ገርፈው፤ አሰቃይተው፤ የያዘውን ነገር ነጥቀው፤ ቢፈልጉ ይለቁታል፤ ወያኔን ማስደሰት ከፈለጉም አንድ አሸባሪ ሊያፈነዳ ሲል ያዝን ብለው ንጹሁን ዜጋ አሳልፈው ይሰጡታል። ያ መከረኛ ወያኔ እጅ ከገባ በኋላ ደግሞ እንደሁኔታው ታይቶ የሆነ ትያትር ይሰራበትና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ይውላል። የአማራ ክልል ታርጋ ያለው መኪና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከተገኘ፤ ፖሊሶች አስቁመው ወዴት እንደሚሄድ ምን እንደሚፈልግ ይጠይቃሉ። ታዲያ አፓርታይድ ከዚህ የተለየ ምን አደረገ?
የደቡብ አፍሪካው የዘረኞች መንግስት፤ ያን ሁሉ ሽንሸናና አፈና፤ ያን ሁሉ ግድያና እስራት ሰብአዊ መብት ረገጣ፤ ያን ሁሉ የመከፋፈል ስልት እየተጠቀመ፤ የደቡብ አፍሪካን ወጣቶች አንድ ሆነው አምርረው አፓርታይድን ታግለው ከማሸነፍና መሪያቸው ማንዴላን ከማስፈታትና ነጻነታቸውን ከመቀዳጀት አልገታቸውም። ልዩነታችን የኛ ዘረኞች አገር በቀል መሆናቸው፤ እነዛኛዎቹ መጤ መሆናቸው፤ የነዛ ወጣቶች በእንድነት ጸንተው እስከመጨረሻው መታገላቸውና የኛ ወጣቶች ደሞ ለራሳቸው የዘረኞቹ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነው፤ እርስ በራሳቸው በድንጋይ መደባደባቸው ነው…… የጋራ ጠላታቸውን ትተው።
የሆነው ሆኖ ኒልሰን ማንዴላ ከተናገራቸውና ለደቡብ አፍሪካ ወጣቶች ጽናትና ብርታት ከሆናቸው ቁም ነገዎች ጥቂቱን ለወጣቶቻችን ልጥቀስና ዛሬ ነገ ሳትሉ አንድ ሁናችሁ አሁኑኑ ተነቃነቁ ልበል…
“ድፍረት ማለት ፍርሀት በሰው ልብ ውስጥ የለም ማለት አለመሆኑን ተምሬአለሁ፤ የራስን ፍርሀት ማሸነፍ እንጂ፤ ጀግና ማለት የማይፈራ ማለት አይደለም፤ ፍርሀቱን አሸንፎ ያሰበውን የሚያደርግ እንጂ!!!””
“በየትኛውም አቅጣጫ ቢሄዱ ወደ ነጻነት የሚደረግ ጉዞ ቀላል አይደለም። ወደምንመኘው ተራራ አናት ላይ ከመድረሳችን በፊት፤ ብዙዎቻችን ደግመን ደጋግመን ሞት ጥላውን በሚያጠላበት ሸለቆ ውስጥ ማለፍ አለብን”
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!
ሞት ለወያኔ!
lkebede10@gmail.com